ታረቀኝ ዘነበ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሥራን ለማስቆም በግብጽ መንግስት ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን መሣሪያነት የዋሉት በርካቶች ቢሆኑም፤ “ድሆች ናቸው” ከሚለው እስከ ማስፈራሪያ ዛቻዎች ድረስ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
በግብፅ በተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ከሙባረክ እስከ
ሙርሲ ብሎም እስከ አሁኑ በፊልድ ማርሻል አል-ሲሲ የሚዘወረው ጊዜያዊ መንግስት ድረስ በርካታ ገዥዎች በትረ
ስልጣኑን ቢቆናጠጡም፤ በዓባይ ውኃ ላይ የሚያራምዱት አስተሳሰብ ግን ልዩነት የተስተዋለበት አይመስለኝም፡፡
ይልቁንም የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን ወደ ጎን በማድረግ የዓባይ ጉዳይ የህዝባቸው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንደሆነ ያለ ልዩነት ሲናገሩ እየተደመጡ ዛሬ ላይ መድረሳቸውን አስረጅ የሚያስፈልገው አይመስለኝም—ሲከውኑት የነበሩት ተግባሮቻቸው አፍ አውጥተው ይናገራሉና። ለህዝባቸው ጥቅም መረጋገጥም ሽንጣቸውን ገትረው መከራከሩን ብሔራዊ አጀንዳቸው አድርገው መቀጠላቸውም እንዲሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራችንን የህዳሴ ጉዞ የማሳካት፣ ሀገራዊውን የፀረ - ድህነት ትግል ከዳር የማድረስ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና ከድህነት መውጫ መሰላል የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመላው ኢትዮጵያዊ የህይወት ጉዳይ መሆኑ ለድርድር የማይቀርብ ቢሆንም፤ በሀገራችን ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን በኩል ብሔራዊ አጀንዳ አድርጎ ከመንቀሳቀስ አኳያ ግን ውጤታማ መሆኑን ለመናገር የሚያስደፍር አይመስለኝም፡፡
ምንም እንኳን ህዝቡ ከግድቡ መሰረተ-ድንጋይ ማስቀመጥ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በዕውቀቱ፣ በገንዘቡ በጉልበቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ ድረስ በመንቀሳቀስ ግድቡን በመስራት ላይ ቢሆንም፤ አንዳንድ የተለየ የፖለቲካ ልዮነት ያላቸው የሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎችና የውጭ ፅንፈኞች ጉዳዩን ሀገራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ከማድረግ ይልቅ፤ ለስልጣን ጥም ማርኪያ መጠቀሚያነት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ የሀገራችንን ህዝብ ግድቡን የመስራት የማይናወጥ አቋምን እንዲሁም የሁሌም ብሔራዊ አጀንዳ መሆኑን ሳይገነዘቡ። እርግጥ ጉዳዮ በቅንነት ሲታይ ከድህነትና ከኋላቀርነት መላቀቅ የማይሻ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብድ ይሆናል። ይሁንና ይህን አሳፋሪ ጉዳይ በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ አጀንዳ አድርገን ለመንቀሳቀስ ያቃተን ለምን እንደሆነ የሁላችንም ምላሽ የሚያሻው ይመስለኛል።
እንደሚታወቀው ሁሉ በዓባይ ውሃ የመጠቀሙ ጉዳይ ላንዱ የቤት፣ የሌላው የጎረቤት ሆኖ በመቆየቱ፤ ለዘመናት የድህነትና የኋላቀርነት መገለጫ ሆነን እንድንሻገር ተገደናል፡፡ በውሃ ሀብታችን እንዳንጠቀም በተጣለብን ገደብም ለተደጋጋሚ ጊዜ በርካታ ዜጎቻችንን በድርቅ ከጉያችን ተነጥቀናል። በዚህም ሀገራችን በውሃ እጥረት ሳቢያ ዜጎች ለሞት የሚዳረጉባት ብቸኛዋ የአለማችን የውሃ ሃብት ባለቤት ሆና ከመቆየቷ ባሻገር፤ የውሃ ሀብቷ የቁጭቷ ምንጭ ብቻ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ግና እነዚህን ሁኔታዎች መቀየር ሀገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ሀገራዊው የፀረ - ድህነት ትግሉን በማቀጣጠል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራን ይፋ አድርጓል፡፡ በእርግጥም የግድብ ግንባታ ለዘመናት የዘለቀውን የድህነትና የኋላቀርነት ታሪካችንን የመቀየርና ያለመቀየር ጉዳይ አንዱ ምክንያት በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳነቱ አያጠያይቅም፡፡
ስለሆነም የግድቡን ግንባታ የማሳካቱ ጉዳይ የአሁኑን ትውልድ ህይወት የመለወጥና ያለ መለወጥ ጥያቄና ውሳኔ ብቻ አይሆንም— የቀጣዩን ትውልድ ህልውና የማረጋገጥና ያለማረጋገጥ ብሎም ሀገራዊ ህልውናን የማስቀጠል ታላቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው እንጂ፡፡ እናም ለሀገራዊ ህልውናችን ቀጣይነት፣ ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ኑሮ መሻሻልና ከድህነታቸው መውጫነት ቁልፍ ሚና የሚጫወተው የህዳሴው ግድብን ብሔራዊ አጀንዳ አድርጎ መስራት የመላው ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ግዴታ መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም፡፡
እንደሚታወቀው ሁሉ የህዳሴው ግድብ ግንባታን ለማስቆም ብሔራዊ አጀንዳቸው አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት የግብጽ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን በዋናነት እ.ኤ.አ በ1978 በቪየና የተፈረመውና የሀገራት ድንበርን የሚወስነው ስምምነት ሊከበር ይገባል የሚል አቋም ሲያራምዱ ይደመጣል፡፡
በእርግጥ ይህ የቪየና ስምምነት የቅኝ ገዥዎች የድንበር አከላለል የማክበር ህጋዊነትን ሀገራት ተቀብለው በሥራ እያዋሉ ቢገኙም፤ ህጉ ድንበርን እንጂ ድንበር ተሻጋሪ ውሃን የሚመለከት ባለመሆኑ ጉዳዩ “ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡
ምክንያቱም ምንም እንኳን አለም አቀፍ የድንበር ስምምነት ቢኖርም፤ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ በአካባቢያዊ ስምምነት የሚፈጸም እንጂ፤ አለም አቀፋዊ ስምምነት የሌለ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግብጾች በመከራከሪያነት የሚያነሱት እ.ኤ.አ. የ1929ና የ1959ኙ ስምምነቶች ከአስራ አንዱ የተፋሰሱ ሀገራት መካከል በሁለቱ ብቻ የተፈረመ ስለሆነ ብዙሃኑን ያላካተተው ስምምነት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡
ይህ ብቻ አይደለም። የግብጽ ፖለቲከኞች ሀገሪቱ በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷ የማይገሰስ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህም “የእኩል ተጠቃሚነት” መርህ የማይታሰብ በሆነበትና በቅኝ ገዥዎች ዘመን አብዛኛውን የውሃውን ባለቤቶች ያገለለና በሁለት ሀገሮች መካከል ብቻ የተፈረመ ስምምነት ስለሆነ፤ ዛሬ አለም እኩል ተጠቃሚነትን መርሁ ባደረገበት ዘመን ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል ብሎ ማሰብ ከየዋህነት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡
እናም ከሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ውጭ እ.ኤ.አ በ2010 በተፋሰስ ሀገራቱ የተፈረመው የትብብር ማዕቀፍ አብዛኛውን በውሃው የመጠቀም መብት ያላቸው ሀገሮችን ያካተተ በመሆኑ ያረጀውና በቅኝ ገዥዎች አማካኝነት የተፈረመው ስምምነት ጉዞ ማክተሙን ያረጋገጠና ተቀባይነቱም የላቀ መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ ለዚህም ነው የግብጾች ጥረት “ልፋ ያለው …” እንደሚባለው የሚቆጠረው፡፡
ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚያውቀው ሀገራችንን ጨምሮ ሁሉም የላይኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በድህነት የሚማቅቁና በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁና ናቸው። በዚህም ሳቢያ በአመዛኙ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ እርዳታ ለመጠበቅ ይገደዳሉ፡፡ ቀደም ሲል ያገኙት የነበረው የዝናብ መጠን ከመቀነሱና በአየር መዛባት ሳቢያ ዜጎቻቸው በረሃብና በእርዛት ለመገረፍ ከመገደዳቸውም በላይ ለእልቂት ተዳርገዋል፡፡
ታዲያ ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ የግብጽ ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙሃን ሌሎችን ከግምት ባላስገባና ስግብግብነት በተሞላው አኳሃን አባይን ለብቻቸው ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት እጅጉን ዘግናኝ ነው፡፡ ምክንያቱም በግልፅ የሚታየው ፍላጎታቸው “እኛ እንብላ፣ እናንተ ግን ተራቡ” የሚል መርህን ማራመድ ነውና፡፡
እናም የህዳሴውን ግድብ መገንባት ግብጾች የህይወታችን መሰረት ነው እንደሚሉት ሁሉ፤ ለኢትዮጵያውያንም ከድህነት የመውጫ ቀዳዳ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በእርግጥ የግብጽ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን የሀገራቸውና የህዝባቸውን ጥቅም ለማረጋገጥ ብሔራዊ አጀንዳቸው አድርገውታል፡፡
በእኛ በኩልስ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለግብፆች የህይወት ጉዳይ እንደሆነ ሁሉ ለኢትዮጵያውያንም ከድህነት የመውጫ ቀዳዳ በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳችን አድርገን ሁሌም መንቀሳቀስ ይኖርብናል።
መቼም ሀገርን ከመውደድ አኳያ ኢትዮጵያውያንን የሚያማ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ያም ሆኖ ግን በእኔ እምነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ እየታወቀ፤ ብሔራዊ አጀንዳ አድርጎ ከመንቀሳቀስ አኳያ ውስንነቶች መኖራቸው አይታበይም፡፡
እርግጥ በአሁኑ ወቅት ያለው እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፤ ጉዳዮን ይበልጥ ወደ ብሔራዊ አጀንዳነት መቀየር ያስፈልጋል ባይ ነኝ። የግድቡ ግንባታ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ብሔራዊ አጀንዳቸው አድርገው እንደሚንቀሳቀሱት ግብጾች ሁሉ፤ ሀገራዊ ጥቅምን የማስቀደም ዜግነታዊና ሙያዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ የሀገራችን ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን የመኖራቸው ሁኔታ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡
ለምን ቢሉ ከግብጾች በኩል የሚሰነዘሩትን የተሳሳቱ መረጃዎች በማጋለጥ፣ የግድቡ ግንባታ ጠቀሜታንና የሚገኝበትን ደረጃ በማሳወቅ ሙያዊና ዜግነታዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ ወገኖችና መገናኛ ብዙሃን በርካታ ናቸውና፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የግብጽ መንግስት፣ ፖለቲከኞችና መገናኛ ብዙሃን የሚሰነዘሩትንና የህዳሴው ግድብ ግንባታን የማይደናቀፍ ጥረት ለማምከን የሀገራችን ምሁራን ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው ለመስራት በመነሳሳት ላይ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ሃቆች በመታየት ላይ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡
ከእነዚህ መካከልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መካከል የተፈረመው ስምምነት አንዱ ሲሆን፤ በምሁራኖቻችን አማካኝነት እየታተሙ ለንባብ በመብቃት ላይ የሚገኙት መጽሐፍቶችም በማሳያነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም የመንግስትና ጥቂት የግል መገናኛ ብዙሃን የህዳሴውን ግድብ ብሔራዊ አጀንዳቸው በማድረግ የተጀመረው ህዝባዊ መነቃቃት ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድ ከማድረግ አኳያ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦም ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው፡፡
ያም ሆኖ ግን ከግብጾች በኩል ካለው እንቅስቃሴ ጋር ሲነጻጸር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን መገንዘቡ ተገቢ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ለሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ስኬታማነት ከፍተኛ ድርሻ የሚያበረክተው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬታማነት በሚደረገው ርብርብ ጉዳዩን ሁሌም ብሔራዊ አጀንዳችን አድርገን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡
ግድቡ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉትና ለሀገራችንም ሆነ ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ተጠቃሚነት ጉልህ ድርሻ የሚያበረክት ነው፡፡ ከዚህ አኳያም ሀገራዊ ፋይዳውን ስንመለከት ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የፀረ - ድህነት ትግል ከግብ በማድረስ ለህዳሴው ጉዞ ስኬት የሚያበረክተው ሚና የላቀ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የሀገራችንን የኤሌትሪክ ሽፋን የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ፤ ለዘመናት መብራት እንደ ገነት ለራቀው የገጠሩ ህዝባችን ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ይህም ለከፍተኛው የደንና የመሬት መራቆት ችግር እንዲሁም ሊከሰት የሚችለውን የአየር መዛባትና የሚያስከትለውን የድርቅ አደጋ የሚያስቀር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሃይል አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለሚደርሰው የጤና ችግር እልባት ይሰጣል፤ መሳ ለመሳም ለህክምና የሚወጣውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ይህም ፋይዳውን ድርብ ድርብርብ ያደርገዋል፡፡
ግድቡ ከዚህም የላቀ ፋይዳ አለው፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ የኤሌትሪክ ሃይልን ለጎረቤት ሀገሮች መሸጥ ይቻላል። ይህም በድህነት ለሚሰቃየው ህዝባችን ህይወትና ኑሮ መሻሻል የሚረዳ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ይሆናል፡፡
እናም ከሽያጩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የሀገሪቱን ዕድገት በማፋጠን ለዜጎች ኑሮ መለወጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡ በመሆኑም የግድቡ ግንባታ በድህነትና በኋላቀርነት የመቀጠልና ያለመቀጠል ጉዳይ ስለሆነ የህልውናችን መሰረት መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላል፡፡
ታዲያ እዚህ ላይ ሊዘነጋ የማይገባው ነገር ቢኖር፤ ሀገራችን ምንም እንኳን ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ የምትከተልና ውጤታማ መሆኗ የሚታወቅ ቢሆንም ቅሉ፤ ወደ ኢንዱስትሪው መር ኢኮኖሚ መሸጋገሯ የማይቀር ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የኤሌትሪክ ሃይልን የሚጠይቅ ነው፡፡
እናም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየተስተዋለ ከሚታየው ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ጋር ተያይዞ ለቀጣይነቱ የህዳሴው ግድብ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ የሚሰጠው ምላሽ ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡
ስለሆነም ወቅታዊውን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከማስቀጠል ባሻገር፤ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምናደርገው ጉዞ መፋጠን አስተዋጽኦው የላቀ ነው—ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ። ለዚህም ነው ግድቡ ለሀገራዊው የህዳሴ ጉዞ ስኬት ዕድገትን የማስቀጠልና ያለማስቀጠል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ እንደ ሀገር የመቀጠልና ያለመቀጠል የህልውና ጉዳይ መሆኑ ተደጋግሞ የሚገለፀው፡፡
እንደሚታወቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይነቱ የዜጎችንና የሀገራችንን ዕድገት በማፋጠን ብቻ የተወሰነ አይደለም—የጎረቤቶቻችንን ተጠቃሚነት በማሳደግ የሰላማችን ዋስትናም ጭምር እንጂ፡፡ እናም ግድቡ ከከፍተኛ የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ለሚሰቃዩት እንደ እነ ኬንያ፣ ጅቡቲና ሱዳን ለመሳሰሉ ጎረቤቶቻችን ለችግራቸው ምላሽ የሚሰጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩተን የሚያሳድግ፣ ግንኙነታችንንም የማጠናከር ሚናው በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡
ይህ ደግሞ የግድቡ ግንባታ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር ለአካባቢው ሠላምና መረጋጋት የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩልም ምንም እንኳን “አንዴ ሌባ ካሉት፣ ቢቆርብም አያምኑት” እንደሚባለው ግብጾች ግትር አቋማቸውን እያራመዱ ቢሆኑም፤ ግድቡ ለእነርሱም ሆነ ለሱዳን የሚያበረክተው አስተዋጽኦን የሚዘነጉት አይመስለኝም፡፡
እርግጥም የግድቡ ግንባታ የውሃውን ፍሰት በማረጋጋት ሁለቱም ሀገሮች ከከፍተኛ የጎርፍና የመጥለቅለቅ አደጋ ሊታደግ የሚችል ከመሆኑ ባሻገር፤ የሱዳኑን የሮሳሪስ ግድብ እንዲሁም የግብጹን አስዋን ግድብ እየተስተዋለባቸው ከሚገኘው የደለል አደጋ የሚታደግ ብሎም ችግሩን ለመቅረፍ ሁለቱም ሀገራት በየዓመቱ የሚያውጡትን ከፍተኛ ወጪ የሚያስቀር ይሆናል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም። የህዳሴው ግድብ ግንባታ በአካባቢያዊ ጥበቃ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው። ለደን መራቆትና ለአፈር መሸርሸር ችግር እልባት የሚሰጥ ስለሆነ ለሀገራቱ ተጠቃሚነት ሚናው የላቀ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
ሆኖም ግድቡ ከሀገራችን ባለፈ ለጎረቤት ሀገሮች የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በዚህ መልኩ የላቀ ሆኖ ሳለ፤ የግብጽ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን ዓባይን መንካት በህልውናቸው ላይ እንደተደቀነ አደጋ አስመስለው በተደጋጋሚ ይገልፃሉ፤ አይነኬነቱንም ይደሰኩራሉ፡፡ ከአጽናፍ አጽናፍም ያስተጋባሉ፡፡
በዚህ ብቻም አይወሰኑም፡፡ የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እናም እነዚህ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የግብጽ ዜጎች ብሔራዊ አጀንዳቸው በማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው፤ ‘እኛስ የሰራነው የሚጠበቀውን ያህል ነውን?’ የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡
ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚያስታውሰው የዘመናት የድህነት ታሪካችንን ለመቀየርና ከተጫነን ድህነት ለመውጣት በምናደርገው ትግል ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው የኢፌዴሪ መንግስት በግድቡ ግንባታ ስፍራ ላይ የመሰረት ድንጋይ ካኖረበት ሰዓት ጀምሮ፤ መላው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለ አንዳች ልዩነት ስኬታማነቱን ዕውን ለማድረግና በራሳችን ተነሳሽነት ማናቸውንም ጉዳዮች ለመከወን ቃል ገብተናል፡፡ በዚህም ሁሉም የሀገራችን ህዝብ የዘመናት ቁጭትና ብሔራዊ ሀብቱ የሆነውን የዓባይ ወንዝን የመጠቀም ምኞትና ፍላጎት በአዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ተደርጓል፡፡
በህዝቦች የማይነጥፈና ሙሉ ተሳትፎ የሚገነባው እንዲሁም የዜጎች ሀብት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በራሳችን ገንዘብና ተሳትፎ የሚገነባ ብቸኛው የዓለማችን ፕሮጀክት ለመሆን በቅቷል፡፡ ዜጎች ከዕለት ምግባቸው ቀንሰው የሚገነቡትና እንደ አይናቸው ብሌን የሚንከባከቡት ግድብ መሆኑም ታሪካዊነቱ የትየሌለ ነው፡፡
እርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በብሔራዊ መግባባት መንፈስ ግድቡን ካለአንዳች ልዩነት በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ለመገንባት ሲነሱ ተርፏቸው አይደለም— በድህነት አለንጋ መገረፉ ማብቃት እንዳለበት በማመናቸው እንጂ፡፡ አዎ! ለስኬታማነቱ ህዝባዊ ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ሲነሱም የማንንም ጉትጎታ ያለመሻታቸው ለድህነት ካላቸው ከፍተኛ ጥላቻ የመነጨ መሆኑም ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም፡፡
እናም መሬት ላይ ያለው ዕውነታ ይህ ሆኖ ሳለ፤ የግብጽ መንግስት ፖለቲከኞች ፣ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን ግን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ጥረት እንደቀጠለ ነው— የውሃው መጠን ስለሚቀንስ የህዝባችንን ኑሮ ለአደጋ ያጋልጥብናል፣ ቅርሳችንን ያፈርስብናል…ወዘተ. የሚሉ ምክንያት ያልሆኑ ምክንያቶችን በመደርደር። እንዲህ ዓይነቶቹን የተሳሳቱ መረጃዎችን በማስተላለፍ ለወቅታዊው የፖለቲካ ትኩሳታቸው ማብረጃ እይተጠቀሙበትም ነው፡፡
እርግጥ ሁሉም የግብፅ ህዝብ በግድቡ ዙሪያ አንድ ዓይነት አቋም
አለው ማለት አይቻልም፡፡ ቀላል የማይባሉ የዚያች ሀገር ዜጎች ቀደም ሲል የገለፅኩትን ዕውነታ
ይጋራሉ—የመንግስታቸውን ማንነት ስለሚያውቁ። ግድቡ ከጉዳቱ ይልቅ ጠቀሜታው የሚያመዝን መሆኑን ምስክርነታቸውንም
እየሰጡ ነው፡፡ የውሃው መጠንም ቢሆን የማይቀንስ ከመሆኑም ባሻገር፤ በተለይ በረግራጋማው አካባቢ የሚተውን
ውሃ የሚያስወግድ ፍቱን መድኃኒት እንደሆነም ይገልፃሉ—ጥናቶችን ማስደገፍ። ይሁንና አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች ሃቁን
ለመቀበል የተሳናቸው ናቸው።
የናይል ተፋሰስ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ7 ነጥብ 10 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር ተጨማሪ ውሃን ማስገኘት እንደሚችል ቢያረጋግጥም፤ ሁሉንም ነገር በጥርጣሬ የሚመለከቱት ፖለቲከኞች የ“ይጎዳናል” ያረጀ አስተሳሰብን በማራመድ ጉዳዩን የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጉት ነው፡፡ ዳሩ ግን ሀገራችን ከምትከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አኳያ ሌሎችን የመጉዳት አስተሳሰብን ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ አታራምድም። ይልቁንም በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የምታምንና ይህንንም በተግባር እያረጋገጠች የምትገኝ መሆኗን በተለያዩ መድረኮች ማስመስከር ችላለች፡፡ ከዚህም መካከል የአባይ ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የኢንቴቤው ስምምነት በማሳያነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ይህን ስምምነት ከዳር ለማድረስ ከአስራ ሶስት ዓመታት በላይ መፍጀቱ ምን ያህል ጥረት እንደጠየቀ ለመረዳት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በአባይ ተፋሰስ የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የነበረው አስተሳሰብን መቀየሩ ብቻ የሚጠይቀውን ጥረት መገመት አይከብድምና፡፡
ያም ሆነ ይህ የግብጽ ፖለቲካዊ ሁኔታ በከፍተኛ ቀውስ በተዘፈቀበት በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን የየራሳቸው አስተሳሰብ ቢያራምዱም በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት ጥረት ግን እምብዛም ልዩነት የማይታይበት ነው፡፡ እዚህ ላይ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር እነዚህ ፖለቲከኞች ፖለቲካንና ሀገራዊ ጥቅምን የሚመለከቱበት መነጽር ለየቅል መሆኑን ነው፡፡ በዚህም ሀገራዊ ጥቅምን የማስከበር ሃላፊነት በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ልዩነት ሊገታ እንደማይገባም ያስገነዘቡን ይመስለኛል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ የእኛ ሀገር አንዳንድ የተቃውሞ ጎራ ፖለቲከኞች አስተሳሰብና ተግባር ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ተቃዋሚ ተብዬው የስልጣን ጥምን የማርካት አባዜው ሀገራዊ ጥቅምን የሚያይበት ዓይን አልፈጠረለትም፡፡ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ልዩነትን ወደ ዳር አስቀምጦ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር መቆም ፈጽሞ የሚያስበው አይመስልም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሁኔታውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመቁጠር በተቃራኒ ጎን የመቆም ሁኔታ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡
እንደሚታወቀው የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ የሀገራችን አንዳንድ ተቃዋሚ ሃይሎች የግድቡን ጠቀሜታ ጠንቅቀው የሚገነዘቡ ሆነው ሳለና የፖለቲካዊ አስተሳሰብ ልዩነቱ ወደ ጎን ትተው ለስኬታማነቱ መረባረብ ሲገባቸው የግብጾችን አቋም ለማስተጋባት ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ ከዚህም አልፎ እንደ ግንቦት ሰባትና ኦነግ የመሳሰሉት አሸባሪዎች የግድቡ ግንባታን በአደባባይ ከመቃወማቸው ባሻገር፤ የግንባታ ሥራውን ለማደናቀፍም እንቅስቃሴ ለማድረግ ቃል መግባታቸው የትናንት ትውስታችን ነው፡፡
በሀገር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ተቃዋሚ ሃይሎችም ቢሆኑ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በበጎ አይን ሲመለከቱ አይስተዋሉም፡፡ እነዚህ ሃይሎች ተቃውሟቸው በህዝቡ ዘንድ ሊያስከትልባቸው የሚችለውን መገለል በማሰብ፤ የግድቡ ግንባታን በግልጽ ባይቃወሙም የተለያዩ ስበቦችን በማቅረብ ግንባታውን እንደማይደግፉ ከማሳወቅ ግን አልቦዘኑም፡፡ አንዴ የህዳሴው ግድብ ግንባታ
ከብሔራዊ መግባባት መቅደሙ ተገቢ አይደለም ሲሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የግድቡን ባለቤትነት ለኢህአዴግ በመስጠት ከፍተኛ መነሳሳት የፈጠረውን ጉዳይ የማደናቀፍ ሴራ ሲሸርቡ ይስተዋላሉ።
ከዚህ ጎን ለጎንም ምንም እንኳን ሰሚ ጆሮ ባያገኙም የእነዚህን ሃይሎች አስተሳሰብ የሚያራግቡ የግል መገናኛ ብዙሃን ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ሥነ - ምግባርንና ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም የሙያ ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ፤ የፅንፈኞች ፖለቲካ አስተሳሰብ ማራመጃ ሆነዋል። ይህን ሃቅ ስንመለከት ‘እነዚህ ወገኖች በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ናቸው?’ የሚል ጥያቄን ከሃፍረት ጋር ያስነሳሉ፡፡
ምንም እንኳን የግብጽ መንግስት ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን የህዳሴው ግድብ የሚያደርሰው ጉዳት እንደሌለ ጠንቅቀው ቢያውቁም፤ ሀገራዊ ጥቅማቸው እንዲከበርና ለብቻ የመጠቀም ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ መሬት ላይ ያለው እውነታ አልገደባቸውም፡፡ ወደ ሀገራችን ስንመለስ ደግሞ ከድህነት መውጫ ቀዳዳና የነገውን ትውልድ ህይወት የተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግረውን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የደህንነት ስጋት እንደሆነ የሚያስመስሉ፣ ከግብጽ መንግስት ጋር መደራደር እንደሚያስፈልግ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ፣ ከህዝቡ ኑሮ ይልቅ ግድቡ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን መገንባቱ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው ብሎም ሀገራዊ ጥቅምን አሳልፈው ለመስጠት ወደ ኋላ የማይሉ ተላላኪዎችን ማየት አዲስ ጉዳይ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ጥቂት ወገኖች በህዝቡ ዘንድ ምንትስ እንደነካው እንጨት የሚታዮ ቢሆኑም። በእኔ እምነት “ቅቤ ምንም ቢበርደው እሳት አይሞቅም” እንደሚባለው የሀገራችን አንዳንድ የተቃውሞ ጎራ ፖለቲከኞችና የፅንፈኞች ልሳን ወደመሆን የተሸጋገሩ መፅሔቶች የጥላቻ ፖለቲካን በማራመድ የሀገር ጥቅምን አሳለፎ የመስጠቱ ተግባርን ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡
ምንም እንኳን በመካከላቸው የማይታረቅ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ቢሆንም ሀገራዊ ጥቅም ግን ሁሉንም የሚያስማማና የጋራ አስተሳሰባቸው ምንጭ በማድረግ ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡
አሊያ ግን የሀገራችን ፖለቲካ ወደ ፊት እንዳይራመድ ደንቃራ በመሆን አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ እናም እዚህ ላይ ከእነዚህ እፍኝ የማይሞሉ ፅንፈኞች ውጪ የግድብ ግንባታ ስኬታማነት የማይናፍቅ ኢትዮጵያዊ ባለመኖሩ ብሔራዊ አጀንዳነቱ ከምንም በላይና ሁሌም መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ በእርግጥም ህዝቡ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ከዕለት ጉርሱና ከዓመት ልብሱ እየቀነሰ ከሚገነባው የህዳሴ ግድብ የበለጠ ብሔራዊ አጀንዳ ሊኖር የሚችል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የህይወት ጉዳይ ነውና፡፡
ስለሆነም የግድቡን ግንባታ ተከትሎ የተፈጠረው ህዝባዊ መነሳሳት ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል፤ መላው የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን መገናኛ ብዙሃን የየድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
እያንዳንዱ ዜጋም በየሄደበት ቦታና በተሰማራባቸው የስራ መስኮች ሁሉ ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የግድቡን ትክክለኛ ገፅታ በማጉላትና የግብፅን አፍራሽ አመለካከቶችን በማጋለጥ ጉዳዩን ሁሌም ብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ የአምባሳደርነት ሚናን መጫወት ይኖርበታል።
No comments:
Post a Comment