Friday, 26 February 2016

ዛሬስ ቢሆን ስለ ብሄር ጥያቄ ብንወያይ ምን ይለናል?



ማህደር ብርሃነ


የመሬት ጥያቄ በኢትዮጵያ የክፍለ ዘመን ጥያቄ ነው። የብሄር ጥያቄም እንዲሁ የክፍለ ዘመን ጥያቄ ነው። እነዚህ ጥያቄዎች የህዝቦች ጥያቄ እንጂ የሊሂቃን ጥያቄዎችም አይደሉም። የሀገራችን የፖለቲካሊሂቃንእነዚህ ሁለቱን ጥያቄዎች በትክክለኛ ባህሪያቸው በመቀበል ወይም በመቃወም አልያም በማንሸዋረር የፖለቲካ ትግላቸው ምህዋር ማድረግ ካልቻሉ ምንም አይነት ስብስብና ፖለቲካ ድርጅት መፍጠር አይችሉም ነበርና ቢያምኑበትም ባያምኑበትም በእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች መጠመቅ የግድ ነበር። ስለሆነም የመሬት ጥያቄና የብሄር ጥያቄ በኢትዮጲያ ትናንትም ዛሬም ነገም የትግል ስበት ማእከል ነበሩ፤ናቸውም፤ ይሆናሉም።




እርግጥ ነው የመሬት ጥያቄ ከብሄር ጥያቄ ፍፁማዊ የሆነ ተዛምዶ የለውም። ይህ ምን ማለት ነው ብለን ፈታ አድርገን እንመልከተው። በአንድ ሃገር የመሬት ጥያቄ አቢይ ጥያቄ ሆኖ የሚከሰተው የብሄር ጭቆና ስላለ ነው ማለት ላይሆን ይችላል። ምንም ዓይነት የብሄር ጭቆና በሌለበት የመደቦች ጭቆና ይኖራል። በኋላቀርና ዋናው የኢኮኖሚ መሰረቱ ገጠር በሆነበት ሃገር የገዢ መደብ ጭቆና የሚከሰትበት ስልተ ምርት ዋናው መሬት ነው። ህዝቦች በእኩልነትና በፍትሃዊነት መሬት ማግኘትና በመሬቱ በሚያፈሱት የጉልበት ጊዜና ሃብት እሴት ያለ ምንም ገደብ መጠቀም የማይችሉበት ሁኔታ ከተፈጠረ የመሬት ጥያቄ የህዝብ ቁልፍ የትግል ጥያቄ ይሆናል።
የመሬትን ጥያቄ በቁልፍ ጥያቄነት አንግቦ የሚነሳ አንድ ብሄር የግድ ብሄራዊ ጭቆናና አድልዎ ላይጫነው ይችላል። ለዚህ ጥሩ መገለጫ የአማራ ህዝብ ነው። በቅድመ 66 አብዮት የአማራ ገበሬ ምንም አይነት ብሄራዊ ጭቆና አልነበረበትም። በቋንቋው ይናገራል፣ በቋንቋው ይማራል፣ በቋንቋው ይዳኛል፣ ባህሉን በተሟላ መንገድ ይጠበቅለታል ይተገብራል። ከመሬት ጥያቄ አንፃር ስንመለከተው ግን ምንም እንኳን እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ወይም የኦሮሞ ህዝብ ጭሰኛ ባይሆንም በመሬትና በምርቱ ላይ ከትግራይ ወይም ከአገው ገበሬ የተለየ ጥቅምና መብት አልነበረውም። እጅግ አሰቃቂ በሆነ ድህነት ይኖር ነበር ብቻ ሳይሆን የገዢዎችን የቁም ተዝካር እንዲያበላም ጭምር እየታዘዘ የግፍግፍ ይፈፀምበት የነበረው የጎጃም ህዝብ ይመሰክራል። ስለሆነም የብሄር ጭቆና የለም ማለት የመደብ ጭቆና የለም ማለት አይደለም። ለዚህም ነው የመሬት ጥያቄና የብሄር ጥያቄ ፍፁማዊ ትስስርም ሆነ ተዛምዶ የላቸውም የሚባለው። ይህ ደግሞ አዲስ የፖለቲካል ሳይንስ ንድፈሃሳብ ግኝት ሳይሆን የቀደሙ ምሁራንና ፖለቲከኞች ብዙ የፃፉበትና ያሉለት ጉዳይ ነው።
1930ዎቹ መጨረሻ የትግራይ ገበሬዎች፣1950ዎቹ መጀመሪያ የጎጃም ገበሬዎች፣ 1960 የባሌ ገበሬዎች አመፆችን ስንመለከት ምንም እንኳን የትግራይና የባሌው የብሄር ጥያቄም ጭምር ባህሪ ቢኖረውም ሶስትም አመፆች ግን የወል ባህሪ ነበራቸው። ሶስቱም መነሻቸው ከገበሬ ማህበረ ኢኮኖሚ መሰረትና ከአጠቃላይ ስልተ ምርቱ የመነጩ የመሬትና በመሬት የመጠቀም የፍትሃዊነት ጥያቄ ናቸው።
ሆኖም በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የመሬት ጥያቄ 90 በመቶ በላይ ከብሄር ጥያቄ ጋር የተጣመረ መሆኑ ግን ሃቅ ነው። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ የመሬት ጥያቄ የብሄር ጥያቄ ገፅታም ጭምር ያለው ነው የሚባለው። ምክንያቱም የኦሮሞን ህዝብ ስንመለከት በመሬቱ ጭሰኛ ነበር። ይህ ሁኔታ መደባዊ ብቻ ሳይሆን ብሄራዊ ጭቆናም ስለሆነ የኦሮሞ ገበሬ የትግል ጥያቄ ከአማራ ገበሬ የትግል ስልት የተለየ መሆኑ የግድ ነበር። በወቅቱ ህዝቡን ለትግል ያነሳሱና ያደራጁ ታጋዮችም ዋናው የትግል ፕሮግራማቸው በብሄር ጥያቄ ላይ ያጠነጠነ ሆነ። ምክንያቱም የመሬት ጥያቄ የመደብ ጭቆና ብቻ ሳይሆን ከዛም በላይ የብሄራዊ ጭቆና መገለጫም ሆኖ ስለ ነበር ነው።
ዛሬ ላይ ሆነን ይህ አጀንዳ እያነሳን ያለነው ሙት ለመውቀስ ሳይሆን ይህንን የሙት መንፈስ በመውረስ የኢትዮጵያ የትናንት እውነታን እንዳይነሳ፣ እንዲድበሰበስ፣ ከዚህ አልፎም አዛኝ ቅቤ አንጓች እንደሚባለው በአማራ ህዝብ ላይ የሆነ ዘመቻ የተከፈተ የሚያስመስል ገፅታ እንዲላበስ በማድረግ ዳግም የአማራ አርሶ አደርንና የዚህ ወገን የሆነውን ህዝብን መሳሪያ ሊያደርጉት እየተፍጨረጨሩ የሚገኙ ሃይሎች ስላሉ ነው። የአማራ አርሶ አደርና ልጆቹ በኢትዮጵያ የነበረው -ሰብአዊ የብሄሮች ጭቆና እንዲወገድ የከፈሉትን መስዋእት ከንቱ ለማድረግና የማይመለከተው አጀንዳ አድርገው ለመሳል የሚሞክሩት የማግለል አካሄድ የነዋለልኝ አፅም እንዳይፈረድባችሁ እንላቸዋለን። በተለይም ወጣቶች 1960ዎቹ ታጋዮችን እነዋለልኝና መሰሎቹ የትግል ፅናትና ህዝባዊነት እንዳይገነዘቡ በአንዳንድ ምሁራን ነን ባዮች የተጀመረው መሰሪ ዘመቻ ተልእኮውን በሚገባ ሊመረምሩት ይገባል።

በመግቢያዬ 1960ዎቹ የህዝብ ንቅናቄ ላይ የነበሩ አስተሳሰቦች በመሰረቱ በሁለት ተቃርኖዎች ዛቢያ የሚሽከረከሩ እንደነበር ገልጫለሁኝ። አንዱ የሃገሪቱ የብሄር ጭቆናን በመካድ የሚነሳ ሲሆን ሌላው ደግሞኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እስርቤት ናትየሚል የእነ ዋለልኝ ደቀመዝሙር ነው። እንደ መኢሶን/የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ/ አይነት መሃል ላይ የሚዋልሉ (መሃል ሰፋሪ) በዘመኑ ቋንቋ ወላዋዮችም ነበሩ። ይህ ልዩነት ኢትዮጵያን ብዙ አስከፍሏታል። ወደ እድገትና ብልፅግና እንዳታመራ ተጨማሪ 17 አመታትም በልቶባታል። በመጨረሻ ረጂሙ የእርስበርስ ጦርነቱ የትኛው አቋም በመያዝ የታገሉትን አሸናፊ እንደሆኑ ሁሉም የሚያወቀው እውነት ነው።
የብሄር ጭቆና አለ የሚባለውን አንቀበልም ብለው ክደው የተነሱ በሂደት እየኮሰመኑ በአንፃሩ የብሄር ጭቆና የኢትዮጵያ ቁልፍ ጥያቄና ማታገያ አጀንዳ ነው ብለው አምነው የተነሱ እየተጠናከሩ መጥተው ደርግን አስወገዱ። በዋነኝነት በኢህአዴግ የሚወከለው ይህ ሃይል ደርግን ለመደምሰስ የቻለው የተለየ የጦር መሪ፣ የተለየ የፖለቲካ እውቀትና ልምድ፣ የተለየ የሰው ሃይል፣ የተለየ ትጥቅና ሎጂስቲክ ስለነበረው አይመስለኝም። ያው የኢህአዴግ መሪዎች አብዛኞቹ የመጀመሪያ ዲግሪም የነበራቸው አይደሉም። የፖለቲካ ልምዳቸውም እዚህ ግባ የማይባል በተማሪው ዩኒቨርስቲ ንቅናቄብለው ተምረው ገናሳይሉ የአብዮት ማእበል ደርሶባቸው በረሃ የወጡ ናቸው። በድርጅቱ የተሰባሰበው ታጋይም ከሌላ ፕላኔት የመጣ ሳይሆን ያው ኢትዮጵያዊ ነው። የትጥቅ ነገር ከተነሳም አንድ ወቅት ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማሪያም ወንበዴ እኛ ባስረከብናቸው መሳሪያ ነው እየተዋጉን ያሉት እንዳሉት የኢህአዴግ ዋና የመሳሪያ ምንጭ የነበረው በምርኮ የተገኘ እንደነበር የደርግም የኢህአዴግም ድርሳናት ይነግሩናል። 1960ዎች የነበረውን የውጭ ድጋፍ እናንሳ ከተባለም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ሲነፃፀር ለምሳሌ ህወሓት ምንም ድጋፍ አልነበረውም ማለት ይቻላል፤ በተለይም በመጀመሪያዎቹ አመታት። በወቅቱ ህወሓት አለም የማያቃት እሷም አለምን የማታውቅ ሚጢጢየ ድርጅት ነበረች። ድጋፍ አገኘች ከተባለ ከኤርትራ ድርጅቶች ነው። በወቅቱ 1967 የህወሐት ታጋዮች ኤርትራ ሄደው ሲሰለጥኑ የኢህአፓና የኢድዩ ታጋዮች ግን ሶሪያ ነበር የሰለጠኑት። የኢህአፓና መኢሶን በወቅቱ ከአለም አቀፍ ታጋዮች ወዳጅነት ሲመሰርቱና በአውሮፓና አሜሪካ የድርጅታቸውን የውጭ ክንፍ እንዲመሰርቱ ሲፈቀድላቸው ህወሐት ግን ገና ከሱዳን አላለፈችም ነበር።
ታዲያ ህወሓት በኋላም ኢህአዴግ ደርግን በመደምሰስ እንዴት ለድል በቁ ቢባል መልሱ ምንም ሚስጢር ያለው አይደለም። ኢህአዴግ ለድል የበቃው ምንም ተአምራዊም ሆነ ምትሃታዊ አቅም ስለነበረው ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች ቁልፍ ጥያቄ የሆነውን የብሄር ብሄረሰቦችን ጥያቄ የማታገያ መስመሩ ስላደረገ ነው። ሌሎች አንድ ምክኒያቶች ቢደረደር ተጨማሪ ከመሆን የበለጠ ድርሻ አይኖራቸውም።

1 comment:

  1. ይሄ ከላይ የተመለከተው ጽሁፍ፤"የመሬትና የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ የክፍለ ዘመን ጥያቄ ብቻ ሣይሆን የህዝብ ጥያቄ ነበሩ እንጂ የሊህቃን ጥያቄ አልነበሩም፡፡ የሀገራችን የፖለቲካ ሊህቃን እነዚህ ሁለቱን ጥያቄዎች የፖለቲካ ትግላቸው ምህዋር ማድረግ ካልቻሉ መፈጠርም ሆነ መኖር አይችሉም ነበር፡፡ ካለ በኋላ ስለሆነም የመሬት ጥያቄና የብሄር ጥያቄ በኢትዮጵያ ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም የትግል ስበት ማዕከል ነበሩ፣ ናቸውም፣ ይሆናሉም ይላል፡፡" ይህ አባባል ውስጡ ሲታይ ቢያንስ ሁለት ግልጽ መልዕክቶችን ያስተላልፋል፡- የመጀመሪያው መልዕክት፣ ካለፉት ጊዜያት ጀምሮ እስከዛሬ የደረሰውም ሆነ ለዛሬዋ ጊዜ ያልበቁ የፖለቲካ አረጃጀቶችና ድርጅቶች የህዝብ ጥያቄ የሆነውን የመሬትና የብሄር ጥያቄዎችን የማታገያ መሣሪያ አድርገው በመጠቀምና በዙሪያው ህዝብን በዋናነትም በፍላጎቱ ማሰለፍ ችለው ነበሩ የሚለው ሲሆን ሁለተኛው መልዕክት ደግሞ ዛሬም ሆነ ነገ እነዚያን ጥያቄዎች የህዝብ ማታገያ መሣሪያ አድርጎ መጠቀም ይችላል፤ይቀጥላልም የሚለው የሆናል፡፡ ከላይ የተጠቀስው የጽሁፉ አካል ያስተላለፈው መልዕክት በአጭሩ አንድ መልዕክት ቢሆንም በሁለት የጊዜ ገደቦች (ከትላንት እስከዛሬ በሚልና ዛሬና ነገም በሚል) ከፍሎ ማየቱ ጥያቄዎቹን የማታገያ መሣሪያ አድርገው የተጠቀሙ፤እየተጠቀሙበት ያሉም ሆነ ወደፊትም ሊጠቀሙበት የሚችሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ቡድኖች ህዝባዊነት ደረጃቸውን ያሳየናል የሚል እይታ አለኝ፡፡ ከዚህ አኳያ በባለፉት ጊዜያት ጥያቄዎቹን እንደማታገያ የተጠቀሙበት የፖለቲካ ድርጅቶች ህዝባዊነታቸውን መገምገሙና ተገቢውን ደረጃ መስጠቱ ጠቃሚና አስፈላጊም ቢሆን ይበልጥ ጠቃሚ የሚሆነው ጥያቄዎቹን እንደማታገያ እየተጠቀሙበትና ወደፊትም ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ ስለሚባሉ ድርጅቶች ማየት በባህሪው ከደረስንበት ወደፊት መጓዝ ስለምሆን በነዚህ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይበጀናል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ ከዚህ አኳያ ጽሁፉን ብንመዝነው ፀሐፊው ማስተላለፍ የፈለገው ወይም ያስተላለፈው መልዕክት ዛሬም ቢሆን የህዝብ ጥያቄ የሆነው የመሬትና የብሄር ጥያቄ አልተመለሰም ማለት ሲሆን ለወደፊቱም ቢሆን እነዚህ ጥያቄዎች የህዝብ ጥያቄነታቸው ይቀጥላል የሚለው መልዕክት ግን ተስፋ የማስቆረጥና የጨለምተኝነት መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ስለሆነም መያዝ ያለበት ጉዳይ በርግጥም ፀሐፊው እንዳሉት እስከዛሬም ድረስ የህዝብ ውግንና በተሟላ ደረጃ የተላበሰ የፖለቲካ ድርጅት ህዝብንና መንግስትን የመምራት ዕድሉን ባለመውሰዱ ምክንያት ጥያቄው ምላሽ አጥቷል፤ እስከዛሬም ተገቢውን ምላሽ በበቂ ሁኔታ ባለማግኘቱ እንደህዝብ ጥያቄ ተንከባልሏል፤ ስለሆነም የማታገያ ጥያቄ ዛሬም በኢትዮጵያችን የብሄርና የመሬት ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄውን በበቂ ሁኔታ መመለስ የሚችል ህዝባዊ ውግንና ያለው የፖለቲካ ድርጅት ኃላፊነቱን ካልተረከበ አሊያም ተልዕኮውን በአግባቡ ፈትሾ ፣ ከስግብግብነትና ለተወሰኑ ወገኖች ከሚያሳይ አድሏዊ አሠራር የፀዳ እንዲሁም በዐውቄትና በምክንያት መምራት ካልቻለ በርግጥም ያ ዘመን የፈጀው ጥያቄ የህዝብ ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን ከመነሻው የህዝብ ጥቅምን ያስቀደመ ድርጅት እስከተፈጠረ ድረስ እነዚህ ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ መልስ የማያገኙበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡
    እስከሁን ከጠቀስኩት የጽሁፉ ክፍል ውጭ ያለው የጸሓፊው አመለካከት ቢታይ ወቅታዊ ባልሆነ ጉዳይ ላይ ጉልበትንና ጊዜን ለማባከን የታሰበ አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ ይህን የምልበትም ምክንያቱ በሌላኛው የጽሁፉ ክፍል የተጠቀሱ ሃሳቦችን በሚመለከት የምስማማባቸው ጉዳዮች የሉም ለማለት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ዓይነት የጽንሰ-ሃሳብ ክርክር ይዘን የኢትዮጵያን የእስከዛሬውን የለውጥ ጉዞ ወደኋላ ወደ 66ቱ አብዮት ደረጃ መውሰድ የለብንም፡፡ ይህ በራሱ አለአግባብ ጊዜንና ጉልበትን ከማባከኑም በተጨማሪ የኢትዮጵያን ህዝብ ትግል የኋሊት እንደመውሰድ ይሰማኛል፡፡ አሁን በተጨባጭ የብሄርና የመሬት ጥያቄ የሚያነሳው ህዝብ ቁጥር እጅግ በርካታ የሆነበት ዋናው ምክንያት ጥያቄው በመሠረቱ ይፈታል ወይንም መልስ ያገኛል ተብል በህዝብ በተጠበቀበት ጊዜ ውስጥ የተሟላ ምላሽ ባለማግኘቱ ያገረሸ ወይንም የእስካሁኑን ትግል ውጤት የመቀልበስ ህደት አሳይቷል፤ እያሳየም ነው፡፡ በተገቢው ሁኔታ ካልተመለሰ በርግጥም የማተገያ ጥያቄ ሆኖ ሊቀጥል የሚችል ቢሆንም በአንጻሩ ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቶችን ትክክለኛ ህዝባዊ ውግንናቸውንም ማሳያ መስተወት ነው ማለትም ይቻላል፡፡ ስለሆነም የውይይቱ ርእስ መሆን የሚገባው የፅንስ-ሀሳብ ክርክር ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ህዝቡ ለጥያቄው ምላሽ አገኛለሁ ብሎ ከጠበቀ በኋላ ምላሽ መስጠት ያልተቻለበት ምክንያቱ ምንድነው? እንዴትስ በአፋጣኝ መመለስ ይቻላል? የሚል መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡

    ReplyDelete