Sunday, 24 January 2016

በዓለም ምድረ ከብድ ቆይታዬ(5)


***Save water and reduce pollution***

 

ትላልቅ ሞሎች የቤጂንግ መገለጫ ይመስላሉ፡፡ እዚህ ሀገርዎ ሆነው እንደሚያስቡት ‹‹ ደግሞ ለቻይና እቃ ብለው›› ጥቂት መቶ ብሮች/ ዩአን ይሉታል የብር ኖታቸው/ ይዞው ወደ እነዚህ ሞሎች ብቅ ቢሉ በሚያይዋቸው እቃዎች ምራቅዎ ሊጨምር ይችላል፡፡ ጠጋ ብለው የተፃፈው ሲመለከቱ ግን አመድዎ ቡን ይላል፡፡ ለአንድ የሴት ሙሉ ልብስ/ ሶስት በአንድ የሚባለው/ 10 ሺህ ዩአን ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ በኛ በሶስት ምቱት፡፡ ወዳጄ እዚህ ‹‹ለዛውም ለቻይና እቃ›› የሚለው አይሰራም፡፡
ከሌለዎት አራት ዩአንዎን /በኛ 14 ብር ገደማ/ ከፍለው በሳቦይ ወደ ሲልክ የሚባለው ገበያ ማምራት ይኖርብዎታል፡፡ በአይን እይታ ባይለይቱም በሞል በሺ ብር የተጠየቁበት እቃ በጥቂት አስር ዮአን ወይም መቶዎች ብሮች ያገኙታል፡፡ አዎ በጂንግ ዛሬም ቢሆን ለአንዱ አልብሳ ሌላውን እርቃኑን የሚሳደር አንጀት የላትም፡፡ በያዙት ሆቴል ለአንድ ምግብ እስከ 300 ዩአን ወይም 900 ብር፣ ለአድ ቢራ 30 ዩአን ወይም 110 ብር ገደማ ሲጠየቁ አረ እሳት የሆነ ንሮ ቢሉ አይፈረድብዎትም፡፡ ግን አይዞት ዞር ዞር ካሉ ቢራን በሶስት ዮአን በርገርም 30 እስከ 15 ዮአን ያገኛሉ፡፡ አንድ ወዳጄ ፓስታን 13 ዮአን መብላቱ ነግሮኛል፡፡ 40 ብር መሆኑ ነው፡፡ የቤት ኪራይ ግን እሳት ነው፡፡ እናም አብዛኛው ነዋሪ ከመሃል ከተማዋ ርቆ ነው የሚኖረው፡፡ የሚበዛው በአምስተኛ ቀለበት ነው የሚኖረው ብለኛለች ስታር፡፡ ፀጉረ ልውጥ ብርቅ በሆነበት ቤጂንግን እንዲህ ስቃኛት ውዬ አልጋየ ላይ ጋደም አልኩኝ፡፡ በራስጌ ያሉ ወረቀቶች አንዱን አነሳሁኝ፡፡ በፍፁም ያልጠበኩት ማሳሰቢያ ተፅፎ አየሁኝ፡፡
እንዲህ የሚል በትህትና የተሞላ የትብብር ደብዳቤም አነበብኩ፡፡

Dear Guest
In an effort to save water and reduce pollution, we will no longer change the bed bin en as a day routine, if you need a change , please put this card on the bed to let us known, we are very pleased to do so.
Tanks you for your cooperation and understanding!
ማሳሰቢያው እያሰላሰልኩኝ ጋደም አልኩኝ፡፡ ሶስት ቀን ቆየሁኝ፡፡ አንሶላው አልተቀየረም፡፡ እኔም እንዲቀየርልኝ አልጠየቅኩም፡፡ ምናለበት ይችን ታህል እንኳን ለቻይና እድገት አስተዋፅኦ ባደርግ፡፡ የሻዎር ጫማ አልተወረወረም፡፡ የተጠቀምኩበት የእጅና የፊት መታጠቢያ ሳመናዬም በቦታው ሰነበተ፡፡ ያለጨረስኩት ሻምፖም በሌላ አልተተካም፡፡ በመሳሳቢያ መሰረት ስምምነቴ መግለፄ አስበዋል፡፡ በአራተኛ ቀን እስቲ ልታዘበባቸው ብዬ ጫማው እላቂ ሳሙናና ሻምፖ ቆሻሻ መጠራቀሚ ላይ ጣልኩት፡፡ በራስጌ ላይም አንሶላ ይቀየርልኝ ብዬ ፅፌ ወጣሁኝ፡፡ ማታ ስመለስ ለትብብርዎ እናመሰግናለን ከሚል መልእክት ጋር ሁሉም ነገር እርሶ እንዳሉት ሆኗል የሚል ትሁት ፅሁፍ አገኘሁኝ፡፡
ቤጂንግ ከደረሱ ሳያዩት የማይመለሱት ትልቅ የአለም ቅርስና የቻይናውያን ገናናት የሚመሰክር ቦታ አለ፡፡ ከመሃል ከተማው የአንድ ሰአት በመኪና ይጓዛሉ፡፡ ቻይናውያን ምድረ ከብዳቸውን በሞንጎላውያን እንዳይደፈር የገነቡት ትልቁ ግንብ ማየት ይኖርብዎታል፡፡ እንዲህ ሲባል ሰምቻለሁኝ፡፡ በተሌቪዥን መስኮትም አይቻለሁኝ፡፡ እንዲያ ያለ ውብ፣ ጠንካራና ማራኪ ደግሞም አጠቃላይ ርዝመቱ 5000 ኪሎሜትር ነው ብዬ ግን እስቤው አላውቅም፡፡ እስቲ አስቡት እንደ ሰባ ደረጃ አይነት ግንባታ 5000 ኪሎሜትር፡፡ ኩራት እራት አይሆኑም ብለው የዛሬዎቹ ቻይናውያን ወደ ብልፅግና ጉዞ እየተምዘገዘጉ ቢሆኑም ታላቁን ግንብ የወረሰ ቻይናዊ በአያቶቹ ለምን አይኮራም፡፡
ቻይናውያን ወኔ ማስታጠቅና ከጀግንነታቸው ቆርሰው ማካፈል እንደሚችሉበት ደግሞ እዚህ ያያሉ፡፡ 5000 ኪሎሜትር ውስጥ እርስዎ ጥቂት ሜትር ደረጃዎች ወጥተው ሲመለሱ ‹‹You are Hero’’ የሚል ሰርትፊኬት ይስጥዎታል፡፡ ስንት ሜትር እንደተጓዙ ባይታወቅም የአሜሪካ ባራክ ኦባማ ይህንን ሰርትፈኬት አግኝተዋል፡፡ እኔም አገኘሁ፡፡ የታላቁ ግንብ ጀግና ተባልኩኝ፡፡ የወጣሁት ግን በጣም ቢጋነን 800 ሜትር ቢሆን ነው፡፡ እኔ ጅግና ከተባልኩኝ 5000 ኪሎሜትር የገነቡና ምድረከብዳቸውን ከወራሪ የተከላከሉ ቻይናውያን ምን ስም ይሰጣቸዋል፡፡
በእለተ እሁድ ቤጂንግን ተሰነብቼ 550 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ያንታይ ለማቅናት ጥዋት ላይ በተዘጋጀልኝ አውቶቡስ ወደ አየር ማረፊያ አመራሁኝ፡፡ ፍፃሜው ባላይም እነ ማሬ ዲባባ ያሸነፉበት የቤጂንግ ማራቶን ጅማሬው በቅርብ ርቀት እየቃኘሁ አለፈኩኝ፡፡ ያንታይ ስንደርስም የከተማው CPC ድርጅት ‹‹ከሁሉም አስቀድሜ ለመናገር እድል በማግኘቴ የተሰማኝ ደስታ እገልፃለሁ›› በሚል ችኮ ፕሮቶኮል አልጀመሩም፡፡ ‹‹ወንድሞቼና እህቶቼ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በቤጂንግ ሴት ልጆቻችሁ በማራቶን አሸንፈዋል›› በማለት ነበር የቅርበት ድልድያቸው የገነቡት፡፡ ቻይናውያን እንዲህ ናቸው፡፡ የሰው ልብ ማግኘትን ያውቁበታል፡፡ ሰማይ የነኩ እንደሚመስሉ ህንፃዎቻቸው መኮፈስን አያውቁበትም፡፡ 45 የአለም ቢሊዮነሮች ያበረከቱ ቤጂንጋውያን መታበይን አይነካካቸውም፡፡ በእራት ግብዣቸው በየ5 እና 10 ደቂቃ ‹‹ጋምቤ አፕ በቶም›› ይልዋችኋል፡፡ በሃገርኛ ለጤናችን እንደማለት ነው፡፡ እንዲህ ሲጋበዙ እርስዎም‹‹ ጋምቤ›› ብለው የወይን ብርጭቆዎን ጭልጥ ማድረግ ይነሩብዎታል፡፡ በያለንበት ‹‹ጋምቤ›› እንባባል ፡፡ ቀጥለን ስለ ሳቂታዎ የብጫ ባህር ፀዳል ያንታይ ወሬያችን እንሰልቃለን፡፡

No comments:

Post a Comment