Friday, 26 February 2016

ዛሬስ ቢሆን ስለ ብሄር ጥያቄ ብንወያይ ምን ይለናል?



ማህደር ብርሃነ


የመሬት ጥያቄ በኢትዮጵያ የክፍለ ዘመን ጥያቄ ነው። የብሄር ጥያቄም እንዲሁ የክፍለ ዘመን ጥያቄ ነው። እነዚህ ጥያቄዎች የህዝቦች ጥያቄ እንጂ የሊሂቃን ጥያቄዎችም አይደሉም። የሀገራችን የፖለቲካሊሂቃንእነዚህ ሁለቱን ጥያቄዎች በትክክለኛ ባህሪያቸው በመቀበል ወይም በመቃወም አልያም በማንሸዋረር የፖለቲካ ትግላቸው ምህዋር ማድረግ ካልቻሉ ምንም አይነት ስብስብና ፖለቲካ ድርጅት መፍጠር አይችሉም ነበርና ቢያምኑበትም ባያምኑበትም በእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች መጠመቅ የግድ ነበር። ስለሆነም የመሬት ጥያቄና የብሄር ጥያቄ በኢትዮጲያ ትናንትም ዛሬም ነገም የትግል ስበት ማእከል ነበሩ፤ናቸውም፤ ይሆናሉም።

Sunday, 14 February 2016

“የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል”







ህዳሴ፡- በቅድሚያ ለቃለምልልሱ ስለተባበሩን በአንባቢያን ስም ከልብ እናመሰግናለን፡፡ በከተማችን የሚ ስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጩ ምንድነው ይላሉ?
አቶ ይስሀቅ፡- እኔም አመሰግናለው፡፡ ከትርጉሙ ስንነሳ መልካም አስተዳደር ዘርፈ ብዙ ትርጉም ነው ያለው፡፡ መልካም አስተዳደር ሲባል የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው፣ ግልፅነት፣ የተጠቃሚነት ስርአት ማስፈን ነው፣ የህዝብ ተሳታፊነትንና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው፣ ዋና ዋና በሆኑት የልማት እና የሰላም ጉዳዮች መግባባት መፍጠር ነው፡፡ እንዲህ ሰፋ ያለ ትርጓሜ ያለው ነው”” በተጨማሪ መልካም አስተዳደር ሲባል መልካም ስራን ከመስራት ይመነጫል”” ህዝቡ የሚጠይቃቸው ጥያቄዎችን አግባብ ባለው መልኩ ህግና ስርአትን በመጠበቅ ፈጣን የሆነ ምላሽ መስጠት ነው”” በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉዳዮችም ህዝቡን በቅንነት ማገልገል ነው፡፡ ህዝብን ማገልገል ክቡር እንደሆነ አስቦ መስራት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነጥቦች በምናይበት ጊዜ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጮችን ስንመለከት ብዙ ናቸው”” ዋና መሰረቱ በየደረጃው ያለ አመራር የተመደበው ህዝብን ለማገልገልና የህዝብ ችግርን ለመፍታት ነው፡፡ የህዝብ ወገንተኛ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት የህዝብ ወገንተኛ ከመሆን ጋር የሚመነጩ ናቸው”” ህዝቡ መበደል፣ መሰቃየት የለበትም የሚል የህዝብ ወገንተኝነት ማጣት ነው፡፡ በየደረጃው ያለ አመራር የህዝብ አገልጋይነት ስሜቱ በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑ ነው፡፡ በየደረጃው ያለው የመንግስት ሰራተኛ የተቀጠረው ህዝብን ለማገልገል መሆኑን በተመለከተ የተሟላ እምነት ይዞ አለመስራት ነው፡፡ ሁለተኛው እላፊ ተጠቃሚነት ነው፡፡ ይህ ማለት የመንግስት እምነት በከተማው ልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መመስረት ነው፣ ይህ ማለት ህብረተሰቡ በየደረጃው የልማቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ፍትሀዊ የሆነ የልማት ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ መፍጠር ነው፣ ስለዚህ ልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ እንደስርአት መመስረት አለበት””  ይህ ማለት አንዱ ተጠቃሚ ሌላው የበይ ተመልካች የሚሆንበት ሳይሆን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃልል ስርአት መፍጠር ማለት ነው፡፡ አሁን በከተማው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቡ በአመለካከትም በተግባርም የበላይ ሆኖ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ትልቅ ፈተና እየሆነ ነው ያለው፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ባይሆንም ህብረተሰቡን የሚያጉላሉት የሚፈልጉት ነገር ስላለ ነው፡፡ በተቀመጠው አሰራርና ህግ መሰረት ከማገልገል ውጪ አገልግሎትን በገንዘብ በጉቦ በመጠየቅ ለመጨረስ የመፈለግ አመለካከት በሲቪል ሰርቪሱም በአመራሩም ስላለ ታግለን ስላላስተካከልን ነው፡፡ ስለዚህ ምንጮቹን በእነዚህ ሁለት መንገዶች መውሰድ እንችላለን፡፡ አንደኛው እላፊ መፈለግ፣ ሁለተኛው እላፊ ባይፈልግም በተቀመጠው አሰራር መሰረት አመራሩና ፈፃሚው ህብረተሰቡን የማገልገል ክፍተት ነው፡፡

Friday, 29 January 2016

በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ሁሌም የማይናወጥ አቋም ያላት አገር- ኢትዮጵያ







ከአሜሳይ ከነዓን
አፍሪካ ህብረት እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 26 ቀን 2001 ዓም ተመሰረተ፡፡ በአፍሪካ አገራት መካከል አንድነትንና መተሳሰብን ለማጎልበት፣ የህብረቱ አባል አገራት ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ፣ በአባል አገራቱ መካከል ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማጎልበት አልሞ የተመሰረት ድርጅት ነው የአፍሪካ ህብረት፡፡ አፍሪካውያን አህጉራቸውንና ህዝባቸውን በሚመለከት ጉዳይ ላይ በጋራ እንዲቆሙ አቅም ለመፍጠር አልሞ የሚሰራው ህብረቱ በአለም አቀፍ መድረክ ላይም የጋራ ትብብር በመፍጠር ለጋር ጥቅም መቆም የሚያስችል አቅምን የፈጠረ ነው፡፡

Sunday, 24 January 2016

በዓለም ምድረ ከብድ ቆይታዬ(5)


***Save water and reduce pollution***

 

ትላልቅ ሞሎች የቤጂንግ መገለጫ ይመስላሉ፡፡ እዚህ ሀገርዎ ሆነው እንደሚያስቡት ‹‹ ደግሞ ለቻይና እቃ ብለው›› ጥቂት መቶ ብሮች/ ዩአን ይሉታል የብር ኖታቸው/ ይዞው ወደ እነዚህ ሞሎች ብቅ ቢሉ በሚያይዋቸው እቃዎች ምራቅዎ ሊጨምር ይችላል፡፡ ጠጋ ብለው የተፃፈው ሲመለከቱ ግን አመድዎ ቡን ይላል፡፡ ለአንድ የሴት ሙሉ ልብስ/ ሶስት በአንድ የሚባለው/ 10 ሺህ ዩአን ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ በኛ በሶስት ምቱት፡፡ ወዳጄ እዚህ ‹‹ለዛውም ለቻይና እቃ›› የሚለው አይሰራም፡፡
ከሌለዎት አራት ዩአንዎን /በኛ 14 ብር ገደማ/ ከፍለው በሳቦይ ወደ ሲልክ የሚባለው ገበያ ማምራት ይኖርብዎታል፡፡ በአይን እይታ ባይለይቱም በሞል በሺ ብር የተጠየቁበት እቃ በጥቂት አስር ዮአን ወይም መቶዎች ብሮች ያገኙታል፡፡ አዎ በጂንግ ዛሬም ቢሆን ለአንዱ አልብሳ ሌላውን እርቃኑን የሚሳደር አንጀት የላትም፡፡ በያዙት ሆቴል ለአንድ ምግብ እስከ 300 ዩአን ወይም 900 ብር፣ ለአድ ቢራ 30 ዩአን ወይም 110 ብር ገደማ ሲጠየቁ አረ እሳት የሆነ ንሮ ቢሉ አይፈረድብዎትም፡፡ ግን አይዞት ዞር ዞር ካሉ ቢራን በሶስት ዮአን በርገርም 30 እስከ 15 ዮአን ያገኛሉ፡፡ አንድ ወዳጄ ፓስታን 13 ዮአን መብላቱ ነግሮኛል፡፡ 40 ብር መሆኑ ነው፡፡ የቤት ኪራይ ግን እሳት ነው፡፡ እናም አብዛኛው ነዋሪ ከመሃል ከተማዋ ርቆ ነው የሚኖረው፡፡ የሚበዛው በአምስተኛ ቀለበት ነው የሚኖረው ብለኛለች ስታር፡፡ ፀጉረ ልውጥ ብርቅ በሆነበት ቤጂንግን እንዲህ ስቃኛት ውዬ አልጋየ ላይ ጋደም አልኩኝ፡፡ በራስጌ ያሉ ወረቀቶች አንዱን አነሳሁኝ፡፡ በፍፁም ያልጠበኩት ማሳሰቢያ ተፅፎ አየሁኝ፡፡
እንዲህ የሚል በትህትና የተሞላ የትብብር ደብዳቤም አነበብኩ፡፡

Friday, 22 January 2016

በዓለም ምድረ ከብድ ቆይታዬ(3)

መቃብሽ ርግበ


 ካዳፍኔ ያመለጠው የምደረ ከብድ ኮሚኒስት ፓርቲ ‹‹Bombard the Headquarter››
***
የትልቅና የታላቋ አገር ቻይና ዋና የፖለቲካ ማእከል ቤይጂንግ የመንግስት ብቻም ሳትሆን የኮሚኒስት ፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ ምክር ቤት ፅ/ቤት መገኛም ነች፡፡
ኮሚኒስት ፓርቲ ቻይና የተወለደው በ1921 እ.ኤ.አ ነበር፡፡ ቻይና ለሶስት አስርት አመታት በርስበርስ ጦርነትና ራሷን ከጃፓን ወራሪ ሃይል ጋር ጦርነት ላይ ያሳለፈች ሃገር ናት፡፡ ኮሚኒስት ፓርቲው በ1949 የኮሚታንት መንግስትን ከቻይና ዋና ክፍል አስወግዶ መንግስትነት ተቆጣጠረ፡፡ ህዝባዊት ሪፓብሊክ ቻይና መሰረተ፡፡ አብዮቱን በመምራትና ሪፓብሊክ ቻይና በመመስረት ማኦ ትልቅ ድርሻ ነበረው፡፡ ነገር ግን በህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ምስረታ ማኦ ፤ ‹‹ቻይና ደካማ ኢንዳስትሪ ነው ያላት፡፡ ገንዘብዋ ትርጉም የለውም፡፡ በከተሞች ስራጥነት ተንሰራፍቷል፣በገጠር የሰብል እጥረት ገጥሟል፡፡ በአንፃሩ የቻይና ህዝብ በአመት በ14 ሚሊዮን እየጨመረ ነው፡፡›› በማለት ያደረገው ታሪካዊ ንግግር ሃገሪቷ በምን ያህል ቀውስ ውስጥ እንደነበረች ያሳያል፡፡

Sunday, 10 January 2016

ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን ለትራንስፎርሜሽን




ዮናስ



 


የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ገና ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ተግባራዊ ሲሆን የሚነካ ሰው፣ ቅሬታውን ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ማስተር ፕላኑን ከኦሮሚያ ጋር የሚያያይዘው ጉዳይ ቢኖር ይሄ ማስተር ፕላን በሚተገበርበት ጊዜ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች ተነጥለው የሚቀሩ ከሆነ፣ ከአዲስ አበባ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም ሳያገኙ ይቀራሉ የሚል እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሲሠራ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች የማስተር ፕላኑ አካል ሆነው ቢሠሩ ከአዲስ አበባ ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ይሄማለት አዲስ አበባ በአዲስ አበባ፣ የኦሮሚያ ከተሞች በኦሮሚያ እየተዳደሩ ማለት መሆኑም ግልጽና የማያሻማ ነው፡፡

Saturday, 2 January 2016

መልካም አስተዳደርን በሁከት ዕውን ማድረግ አይቻልም!

ሰይፉ በቀለ


የመልካም አስተዳደር ያለመረጋገጥ ጉዳይ ለአንድ ወገን የሚተው አይደለም። ይህ ወገንም ጉዳዩን ‘ፈፅሟል’ ወይም ‘አልፈፀመም’ በማለት ክንዋኔውን ብቻ እንዲያሂድ መጠበቅ የለበትም። ይልቁንም የችግሩ ክስተት ሁላችንም ኃላፊነታችንን በሚገባ ባለመፈፀማችን ሳቢያ የሚከሰት በሽታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እርግጥ ልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስታችን በሀገራችንን ያለውን ልማት በማፋጠን በፍላጎት መስፋት የሚፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ላለፉት ዓመታት ደረጃ በደረጃ እየፈታ መምጣቱ አይታበይም፡፡ በአሁኑ ወቅትም ይህን ወሳኝ ተግባር ይበልጥ ዕውን ለማድረግ በመትጋት ላይ ይገኛል።
ህዝቡም ይህን የመንግስትን ክንዋኔ በሚገባ እየተገነዘበ መጥቷል። ልማቱን ከሚመራው መንግስት ጎን በመቆምና የልማት አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆን በርካታ ተግባራትን እየከወነ ይገኛል፡፡ እርግጥ በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው ሁለንተናዊ ዕድገትና ለውጥም መሰረቱ ህዝብ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ታዲያ ህዝብ ያልተሳተፈበት ማንኛውም ዓይነት ልማት ስኬታማ መሆን እንደማይችል የሚገነዘበው መንግስት፣ ከህዝብ ጋር በመሆን በርካታ ግዙፍና “አይከናወኑም” የተባሉ ተግባራት እየፈፀመ መጥቷል። ውጤትም አግኝቷል።
ይህ የመንግስትና የህዝብ የተቀናጀ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ በአንዳንድ የስነ-ምግባር ችግር ባለባቸው አመራሮችና ፈፃሚዎች የሚከናወኑ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ህዝቡን ለከፋ ምሬትና ጉስቁልና እየጋበዙት መሆኑ በተግዳሮትነት የሚታይ ነው። እናም መንግስት እነዚህን ተግባራት በቀላሉ አላለፋቸውም፡፡ ቁርጠኛ አቋምም እየያዘባቸው ነው።
በዚህም ሳቢያ በአገልግሎት አሰጣጥ መዛባት የሚፈጠሩ የህዝብ ቅሬታዎችን ደግሞ አመራሩ በየዕለቱ በመገምገምና ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያጋልጡ አሰራሮችን በመፈተሽ፣ የተጠያቂነት ስርዓቱንም በጥብቅ ዲስፕሊን በመምራት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት ቆርጦ ተነስቷል፡፡ በመሆኑም ልማታዊው መንግስት ሁሉን አቀፍ ተግባራትን ገቢራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። በተለይም የጥገኝነት፣ የጠባብነትና የኪራይ ሰብሳቢነት መታጎሪያ የሆነውን የመልካም አስተዳደር ችግርን በመፋለም ጊዜያዊ ችግሮች ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው።
እርግጥ መልካም አስተዳደር የአንድ ጀንበር ስራ አይደለም። በጊዜ ዑደት ውስጥ ሊፈታ የሚችል ተግባር ነው። ሰሞኑን በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ የተከሰተው ሁከትም ይሁን ሌሎች በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ነባራዊ ችግሮች በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ታይተው እልባት እያገኙ የሚሄዱ ይሆናል። ይሁንና አንዳንድ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ተግባሩን መንግስት በምክንያትነት የሚጠቀመው በማስመሰል ላለመቀበል ይዳዳቸዋል።
ሁላችንም እንደምንገነዘበው ግን መልካም አስተዳደር ተግባሩ ተቃዋሚዎች “መንግስት ባለፉት ዓመታት መልካም አስተዳደርን አላሰፈነም” እያሉ እንደሚያስወሩት ሳይሆን የራሱን ሂደት ጠብቆ በጊዜ ዑደት ውስጥ የሚገነባ ተግባር ነው። ተግባሩ በሂደት እንጂ በአንድ ጀምበር የሚመጣ አለመሆኑን ነው። ምዕራባውያንም ቢሆኑ ዛሬ ለደረሱበት የመልካም አስተዳደር ተግባር ረጅም ጊዜ የወሰደባቸው መሆኑን መገንዘብ ያሻል። በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ያለ ጀማሪ የዴሞራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ አራማጅ ሀገር፤ ተግባሩን “በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ካላመጣች” ብሎ በጭፍን መሞገት ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ነው።
ላለፉት 24 ዓመታት መልካም አስተዳደር በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ውስጥ ስር እንዲሰድ ዘርፈ ብዙ ጥረት አድርገዋል። በመሆኑም በተቃዋሚዎቹ ለመቃወም ብቻ የሚሰነዘሩ ሃሳቦች እነዚህን ጥረቶች የሚወክሉ አይደሉም። መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፤ አጥጋቢ ውጤቶችም ተገኝተዋል።
የሀገራችን ዴሞክራሲ ስር መስደድ ይችል ዘንድ በሁሉም ደረጃዎች የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲቋቋሙና እንዲጠናከሩ፣ የዳበረ የፍትህ ስርዓት እንዲገነባ፣ የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲጎለብት፣ በየደረጃው ባሉ የመንግስት አካላት ውስጥ የግልፅነት፣ የተጠያቂነትና የህዝብ አገልጋይነት መርህ እንዲሰፍንና የተግባር መመሪያ እንዲሆን ብሎም በሁሉም መስኮች የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ…ወዘተ ብርቱ ጥረት ተደርጓል።
ይሁንና የተቃውሞው ጎራ ግን የተከናወኑትን በጎ ተግባሮች ግምት ውሰጥ ሳያስገባ በጭፍን የህግ አስፈፃሚውን አካል በደፈናው ለማውገዝ መሯሯጡ ከትዝብት ውጪ የሚያተርፍለት አንዳችም ነገር ያለ አይመስለኝም። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱን አንድም ስንዝር ፈቅ ሊያደርገው ስለማይችል ነው። ለምን ቢባል፤ ጭፍን ጥላቻ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትን እንጂ ዴሞክራሲያዊነትን ሊወልድ ስለማይችል ነው። የሀገራችን የህግ አስፈፃሚ አካል ተቃዋሚዎቹ እንደሚያስደምጡን የጥላቻ አሉባልታ ዲስኩር ሳይሆን፤ በህግና በህግ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ የሚመራና የሚሰራ ነው።
በመሆኑም አባሎቻቸው በወንጀል ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር ሲውሉ “የህግ የበላይነት የለም” እያሉ የሚያላዝኑት ተቃዋሚዎች ይህን ሃቅ ሊረዱት ይገባል። ምክንያቱም በህግ ጥላ ሰር የሚገኝ ማንኛውም ታራሚ ህጉ የሚፈቅድለትን ነገሮች ሁሉ ከማከናወን የሚያግደው አንዳችም ነገር ስለሌለ ነው። ይህም የመልካም አስተዳደር ቁልፍ መርህ የሆነው የህግ የበላይነት ያለምንም መሸራረፍ ገቢራዊ ለማድረግ ታስቦ የሚከናወን ነው። በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ ለአንድ ወይም ለሁለት አባሎቻቸው ተብሎ የሚቀለበስ የህግ የበላይነት ሊኖር እንደማይችል ማወቅ ያለባቸው ይመሰለኛል።
እንደሚታወቀው በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ አስፈፃሚው አካል በማንኛውም መስፈርት ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ምናልባትም እንዲህ ዓይነቱ ጣልቃ ገብነት ተቃዋሚዎቹ በሚያራምዱት ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ውስጥ ገቢራዊ ሊሆን ይችላል። ሀገራችን በተያያዘችው ደዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ግን እንኳንስ ሃሳቡን ገቢራዊ ማድረግ ቀርቶ ማሰብም አይቻልም። ምክንያቱም የመንግስት ፖሊሲና አሰራሮች ለጥቂት ግለሰቦች አሊያም ሌላውን ወገን ላለማስከፋት ሲባል የሚለወጡ ባለመሆናቸው ነው።
እርግጥ የመንግስት አካላትና ሃላፊዎች ፖሊሲዎቻቸውን በየቀኑ የሚቀያይሩ ከሆነ ህዝብ የጣለባቸውን አደራ ይወጣሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ለነገ ብለው የሚያቅዱት ነገርም አይኖርም። ዳሩ ግን የህግ የበላይነት ሲኖር፤ ህጎች በምክር ቤት ውይይት አማካኝነት ፀድቀው ካልሆነ በስተቀር በየቀኑ አይቀያየሩም። ማንኛውም ሰው በእነዚህ ህጎች ስር ሆኖ ስለሚሰራና ህጎቹንም የሚተላለፍ ስለሚቀጣ ከህግ ውጪ እንዳሻው የሚሆን ዜጋ ሊኖር አይችልም። በመሆኑም የህግ ልዕልና ይረጋገጣል ማለት ነው።
የህግ የበላይነት በታወቀ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ የሚሰራበት መሰረታዊ የዴሞክራሲ መርህ መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ያሻል። ምክንያቱም የህግ የበላይነት በየጊዜው በመንግስት ወይም በግለሰቦች የሚጣስ ከሆነ፤ ጅምር ዴሞክራሲያችን አደጋ ላይ መውደቁ ስለማይቀር ነው። ዳሩ ግን ከተቃዋሚዎቹ በስተቀር ህዝቡም ሆነ መንግሰት ታዳጊው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲደናቀፍ አይፈልጉም። እናም ዴሞክራሲያዊ አሰራርን የኢ-ዴሞክራሲያዊ ካባ ደርበው የሚንቀሳቀሱት ተቃዋሚዎች ይህ በህዝቡ የማይደገፍ እኩይ ሴራቸው “ላም አለኝ በሰማይ… ” እንዲሉት ዓይነት መሆኑን ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል።
ልክ እንደ ሌሎቹ የዴሞክራሲም ይሁን የልማት ተግባራት መልካም አስተዳደር የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት በመንግስት ጥረት ብቻ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል መሆኑ ነው—ማንኛውም ህዝብ ያልተሳተፈበት ጉዳይ ተፈፃሚ ሊሆን አይችልምና። በመሆኑም በመንግስት በኩል መልካም አስተዳደርን ዕውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉና በሂደት የሚከናወኑት ቁርጠኛ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው፤ መላው ህዝብም ዛሬም እንደ ትላንቱ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይኖርበታል።
በተለይም ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት በሚባሉት እንደ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዓይነቶችን በአግባቡ በመጠቀምና የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከታትሎ በማሳወቅ ለመልካም አስተዳደር እመርታ መትጋት ከማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው።
መንግስት ምንም እንኳን ግዴታው ቢሆንም ህገ-መንግስቱ በሚያዘው መሰረት ብሎም ራሱም ለዴሞክራሲ ስር መስደድ ካለው ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት፤ መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና የዜጎች አቤቱታ የሚደመጥበት እንዲሁም ተገቢው ምላሽ የሚሰጥበት የእንባ ጠባቂ ተቋምን አቋቁሟል። እናም ለዴሞክራሲው ግንባታ እውን መሆንና ላሳየው የማይናወጥ ቁርጠኝነት “አበጀህ” ሊባል ይገባል እንጂ፤ ያለ አንዳች ማስረጃ በመንግስትና በተቋሙ ላይ በደፈና ጥላቻ እየታገዙ የውርጅብኝ መዓት ማውረድ ተገቢ አይመስለኝም። ክንዋኔዎችን በአንክሮና በሰከነ አዕምሮ ከሚያይ ፓርቲ የሚጠበቅም አይደለም።
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የዜጎችን አስተዳደራዊ በደል ተገቢው ምላሽ እንዲያገኝ በርካታ ስራዎቸን በማከናወን ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ እየታወቀ፤ በስሜት ብቻ እየተገፋፉ የተቋሙን ስም ለማጥፋት መሯሯጥ እንዲሁም የመንግስት በዘርፉ እያደረገ ያለውን ጥረት በፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ታፍኖ ላለመቀበልና ለማጣጣል መሞከር “ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ” ዓይነት በመሆኑ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም። ራሱ ተቃዋሚ ነኝ ባዩ አካልም ቢሆን አመለካከቱ ገንቢና ዴሞክራሲያዊ ባለመሆኑ በእንዲህ ዓይነቱ ጭፍን እሳቤ ጉዞው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ አሜኬላ እሾህ ሊሆን እንደሚችል ማወቅ ያለበት ይመስለኛል። እንዲህ ዓይነቱ እሳቤ የትም የሚያደርስ አይደለምና! እርግጥ ይህን መሰረታዊ ሃቅ የማይቀበል ማንኛውም ወገን ለማን ብሎ እንደሚከራከር በቂ ግንዛቤ አለው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው።
መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የንድፈ-ሐሳብ ጉዳይ አይደለም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ተግባሩ ከዜጎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ፤ በአተገባበሩ ላይ የስልጣኑ ባለቤት የሆነው ህዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለበት። ይህም ህዝቡ በህገ-መንግሰቱ የተጎናፀፈውን ስልጣን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ዕድል ይፈጥራል።
ታዲያ የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ይህ ሁኔታ እንዲተገበር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ቀደም ሲል የጠቀስኩት የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ችግሮችን እየተከተታተሉ በማረም ለመልካም አስተዳደር ግንባታው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ከተቋቋሙት ገለልተኛ አካላት ውስጥ ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ናቸው።ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ እነዚህ አካላት እንዲቋቋሙ በአዋጅ ከማፅደቅ ጀምሮ፤ ተግባራቸውንም የመልካም አስተዳደር ዕመርታን በሚያረጋግጥ አኳኋን እንዲፈፅሙ እስከ ማድረግ ድረስ አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።
እነዚህ ገለልተኛ አካላት ህዝቡ በህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጡለት መሰረታዊ መብቶቹ ተግባራዊ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። እስካሁንም ድረስ በርካታ ህዝባዊ ጉዳዮችን በመመልከት የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት እየተወጡ ነው—አቅም በፈቀደ መጠን። የመልካም አስተዳደር ስራ በርካታ ዓመታትን የሚጠየቅ ከመሆኑም በላይ፤ሀገራችን ካለባት የማስፈፀም አቅም ውስንነት አኳያም ተያይዞ የሚታይ ነው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ያለው የመልካም አስተተዳደር ትግበራ አፈፃፀም የአቅም ውስንነትን ተሻግሮ መሻሻል እያሳየ ነው።
ይህ ማለት ግን ፈፅሞ የመልካም አስተዳደር ችግር የለም ማለት አይደለም። በአስቸኳይ መፈታት ያለባቸው ችግሮች በአፋጣኝ መፍትሔ እየተሰጣቸው ነው። ሌሎችም እየታዩ በሂደት ምላሽ ያገኛሉ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ማንኛውም የመልካም አስተዳደር ችግር በሂደት የሚስተካከል ነው። ሆኖም እንደ ተቃዋሚዎቹ ሁሉንም ነገር የመደፍጠጥ አባዜ ‘ምንም አልተሰራም’ የሚል ዲስኩር ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም በተጨባጭ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ህያው አብነቶች ናቸውና።
እንደሚታወቀው በእኛ ሀገር ዕውን በሆነው ባልተማከለው ፌዴራላዊ ስርዓት መሰረት፤ ህዝቡ የፖለቲካ መሪዎቹንና ተወካዩቹን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ ድረስ ይሾማል፤ይሽራል። ህዝቡ በምርጫ ካርዱ አማኝነት በቀጥታ የስልጣን ባለቤት የሆነበት ይህ አሰራር በስርዓቱ ውሰጥ ወሳኝ ሚና ቢኖረውም፤ በህዝቡ በቀጥታ የማይመረጡና ሊመረጡ የማይችሉ አካላት መኖራቸው አይቀርም። በዚህ የአሰራር ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቀሱት ስራ አስፈፃሚው ሲቪል ሰርቪሱና የዳኝነት አካላት ናቸው።
እነዚህ አካላት ለመልካም አስተዳደር አተገባበር ያላቸው የማይተካ ሚና ስለሚታወቅም፤ እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር በምክር ቤቶች የሚሾሙ ወይም ለምክር ቤቶቹ ተጠሪ ይሆናሉ። ሆኖም ግን የየራሳቸው ነፃነት ያላቸው አካላት መሆናቸውን መዘንጋት አያስፈልግም። በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ ስራ አስፈፃሚውና ሲቪል ሰርቪሱ ማንም እንዳሻው የሚፈነጭባቸው አካላት አለመሆናቸውን ማወቅ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ይልቅ ህዝቡና የህዝቡ ተወካዩች በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መክረው ያፀደቋቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ህጎች በተሟላ ሁኔታ የሚያስፈፅሙ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ያለ አድልኦ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ተቃዋሚዎቹ እየመረራቸውም ቢሆን መቀበል አለባቸው። ምክንያቱም እነዚህ አካላት ይህን በማድረጋቸው የህዝቡ ሉዓላዊነት መሳሪያዎች፣ አገልጋዩችና የመልካም አስተዳደር ፈፃሚዎች ከሆኑ በርካታ ዓመታትን በማስቆጠራቸው ነው።
የሲቪል ሰርቪስ ስርዓቱ የተጠቃሚው መብትና ጥቅም እንዳየሸራረፍ እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በርካታ ተግባባራትን አከናውኗል። ይህ ተግባርም መንግስት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መተኪያ የሌለው ድርጊት መሆኑን እንደሚያምንና በቁርጠኝነት ለመተግበርም በሃላፊነት ስሜት መንቀሳቀሱን የሚያመላክት ነው።
ከዳኝነት ስርዓቱ ጋር በተያያዘም ህዝቡ በተወካዩቹ አማካኝነት ያፀደቀውን ህገ-መንግስትና ይወክሉኛል ባላቸው አካላት አማካኝነት የሚወጡ ህጎችን በትክክል መተርጎሙ፣ በዚህ መሰረትም አቅም በፈቀደ መጠን ለባለ ጉዳዩ ፈጣንና ትክክለኛ ፍትህን ያለ አንዳች አድልኦ ስር በመስደድ ላይ ነው።
ታዲያ እዚህ ላይ ከሀገራችን ለጋ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት አኳያ ሲቪል ሰርቪሱም ይሁን የዳኝነት ስርዓቱ ፍፁማዊ ደረጃ ላይ ደርሰዋል እያልኩ አለመሆኔን ውድ አንባቢዎቼ እንዲገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ። ዴሞክራሲው ገና ጅምር በመሆኑ ካለፉት ስርዓቶች የወረስናቸው የተለያዩ አመለካከቶች እንቅፋት መፍጠራቸው አይቀሬ ነው። ይሁንና መንግስት ይህን ሁኔታ ለመቅረፍ ችግሮቹን በአፋጣኝ ለመፍታት በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል።
የሰለጠነ የሰው ሃይልን በመፍጠርና ስርዓቱ የሚፈልገውን የስራ አስፈፃሚና የህግ ተርጓሚ አካላትን ዕውን ለማድረግ የማስፈፀም አቅምን በመገንባት ረገድ የወሰዳቸው ወሳኝ እርምጃዎች ተጠቃሽ ናቸው።
የሰው ሃይልን በተግባር ሂደት የማብቃት፣ አሰራርና አደረጃጀትን ለማሻሻል የሚያስችል የሲቪል ሰርቪስና የፍትህ አስተዳደር ማሻሻያ ተቀርፆም ወደ ተግባር በመግባት ከፍተኛ ውጤት ተገኝቶበታል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ሊያሰራ የሚችልና ወደፊት የሚጎለብት የማስፈፀም አቅምን በሲቪል ሰርቪሱና በዳኝነት ስርዓቱ ውስጥ ለመገንባት ተችሏል። ይህ ጥረት ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
እርግጥም ቁርጠኝነት እስካለ ድረስ የመልካም አስተዳደር ችግር በእርግጠኝነት መፍትሄ ሊያገኝ የሚችል ችግር ነው፡፡ ለተግባራዊነቱ ቁርጠኝነቱና ጽናቱ በእርግጥ ካለ የመልካም አስተዳደርን ችግር ያለጥርጥር መፍታት ይቻላል፡፡ መልካም አስተዳደር ማለት ውሳኔን የማሳለፍና ተግባራዊ የማድረግ ሂደት ነው፡፡ ውሳኔ ማሳለፍ ሲባል፣ ፍፁምነት ያለው፣ ስህተት የሌለበት፣ ትክክለኛ የሆነ ማለት ሳይሆን ካሉት የውሳኔ ሃሳቦች መካከል በተቻለ መጠን ከአገሪቱ አቅም፣ ከህዝቡ ፍላጐት፣ ከሚጠበቀው የዕድገት ውጤት… ወዘተ. ጋር ሲታይ ተገቢው የሆነውን ውሳኔ ለማሳለፍ የተሻለ ሂደትን የተከተለ አሰራር ማለት ነው፡፡
አሰራሩን በሂደት ለመከተል ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለባቸው የመልካም አስተዳደር መርሆዎች አሉ፡፡ ለመልካም አስተዳደር ውጤታማነት ዋናውና እጅግ በጣም አስፈላጊ መሳሪያ ተጠያቂነት ነው፡፡ የፌዴራሉም ሆነ የክልል መንግሥታት በሚያስተዳድሩትና በሚወክሉት ህዝብ ስም ለሚያሳልፉት ውሳኔ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ሪፖርት ማቅረብ ብቻ በቂ አይመስለኝም፡፡ ባሳለፉት ውሳኔ ምክንያት ለተፈጠሩ ችግሮችና መስተጓጉሎች መጠየቅና መልስ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡
ሌላኛው የመልካም አስተዳደር ውጤታማነት መርህ ግልጽነት ነው፡፡ ዜጐች የውሳኔ አሰጣጡን ሂደት አስፈላጊነትና ተመራጭነት መረዳትና መከታተል ይኖርባቸዋል፡፡ ይኸውም መንግስት ያሳለፈው ውሳኔ እንዴትና ለምን እንደሆነ በግልጽ ማየት መቻል ይኖርባቸዋል፡፡ ውሳኔ የተሰጠው በየትኛው መረጃ ላይ ተመስርቶ እነማንን አማክሮ ፣ በየትኛው የህግ አግባብ ላይ ተመስርቶ እንደሆነ ዜጐች በግልጽ ሊያውቁ ይገባል፡፡ ዜጐች ይህን ካላወቁ ማንም ሹመኛ እንደፈለገው ውሳኔ እየሰጠ የህዝቡን ፍላጐት ሊበጠብጥ ይነሳል፡፡ እናም ግልጽነት ወሳሽ ጉዳይ ነው፡፡
ሌላኛው የመልካም አስተዳደር መርህ የህግ የበላይነት ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ሁሌም በህጉ መሰረት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ በፌዴራሉ መንግሥት፣ ወይም በአስፈፃሚ አመራሮች ወይም በክልሎች ደረጃ የሚተላለፉ ውሳኔዎች የአሰራር ሂደታቸው በሀገሪቱ ህግጋት መሰረት የተከናወኑ መሆናቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የሚከናወኑት ማናቸውም ተግባራት የሀገሪቱን ህገ-መንግሥት እና እርሱን ተከትለው የወጡ ህጎችን የተከተሉ መሆን አለባቸው።
የትኛውም ወገን ከመሬት ተነስቶ ከህግና ከአሰራር ውጪ የራሱን ህግ እያወጣ ወይም የህጉን ትርጉም እያጣመመ ወይም ሆን ብሎ እየጣሰ ውሳኔ ሊሰጥ ወይም በሌላ አካል ላይ ተጽዕኖ በማሳደር እስከ ቀበሌና ወረዳ ድረስ እጁን እያስገባ የፈለገውን ሰው በዘመድ፣ በአገር ልጅነት ወይም በሌላ የጥቅም ግንኙነት ሊጠቃቀም አይችልም፡፡ ሁሉም ዜጋ በህግ-ፊት እኩል መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ ሁሉም ዜጋ ሀገሪቱ ከምታመነጨው በረከት እኩል ተጠቃሚ መሆኑን እያሰበ መወሰን ይኖርበታል፡፡ ይህም ሲሆን የህግ የበላይነት ይበልጥ እየተረጋገጠና በህጉና በህጉ አግባብ ብቻ እውን እየሆነ ይሄዳል።
ሌላኛው የመልካም አስተዳደር መርህ ምላሽ ሰጪነት ነው፡፡ እንደ ማዕከላዊም ሆነ እንደ ክልል መንግሥትነቱ ሁልጊዜም መጣር ያለበት የሁሉንም ህብረተሰብ ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡ በህብረተሰቡ ጥያቄ ውስጥ የተለያዩ ተወዳዳሪ ፍላጐቶች ቢኖሩም እነዚህን ፍላጐቶች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በተገቢው ጊዜ ውስጥ ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ምላሹም ወቅታዊ መሆን አለበት። ወቅቱን ያልጠበቀ ምላሽ አግባብነቱ ላይ ጥያቄ ማጫሩ አይቀሬ ነው።
መልካም አስተዳደር ሁሉንም ያቀፈና በእኩል ለመመልከት የመቻል ባህርይ አለው፡፡ በውሳኔ ሂደት ውስጥ የሁሉም ህዝብ ፍላጐት መታየት ወይም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ የትኛውም ወገን በተለይም በአንድ ክስተት ውስጥ ተጎጂ የሆኑ ዜጎች በውሳኔ አሰጣጡ ወቅት ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
መልካም አስተዳደር ውጤታማና ብቃት ያለው ሊሆን ይገባል። ያለውን የሰው ሀብት፣ የግብአት ዓይነትና ጊዜውን በተቻለ መጠን ለህብረተሰቡ የተሻለ ውጤት እንዲያስገኙ የሚያስችል የውሳኔ አሰጣጥና አተገባበር ሂደትን የተከተለ መሆን አለበት፡፡
እርግጥ መልካም አስተዳደር ውጤታማ የሚሆነው አሳታፊ ሲሆን ነው፡፡ ህብረተሰቡ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በሚተላለፉ ውሳኔዎች ውስጥ ሁሉ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ህዝብ እንዲሳተፍ መደረግ ይኖርበታል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያለውን ሃሳብ አውጥቶ ማቅረብ አለበት፡፡ ያሉትን ችግሮች በአደባባይ እንዲገልፅ ሊበረታታ ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ተገቢውን መረጃ ሊያገኝ ይገባል፡፡
ህዝቡ በተወካዮቹ አማካይነትም የውሳኔ አሰጣጡ ሂደቱ አካል መሆን መቻል አለበት፡፡ አሳታፊነት ሲባል ለተወሰኑ ቀናት ህዝቡን ሰብስቦ ማንጫጫትና ‹‹አሳትፈናል፣ አወያይተናል›› ማለት ሳይሆን የህዝቡን ሃሳብ እንደ ግብአት በመውሰድ ለተግባራዊነቱ መትጋትን የሚጠይቅ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የአሳታፊነት መገለጫ ሌሎች አካላትንም ለምሳሌ የተለያየ ህዝብ አደረጃጀቶችን፣ ሲቪክ ማህበራትን፣ የሰብዓዊ መብትና የእንባ ጠባቂ አካላትን በተለይ ነፃ ሚዲያውን ያጠቃለለ መሆን አለበት፡፡ ከእነዚህ አካላት የሚመጡ ሃሳቦች ለመልካም አስተዳደር ሥርዓት መሰረት ታላቅ ግብአት እንደሚሆኑ መታመን አለበት፡፡
እዚህ ላይ ከአሳታፊነት አንፃር የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤትን ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል። እንደሚታወቀው እንደሚታወቀው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዴሞክራሲያዊ ፓርላማን ይወልዳል። በህዝብ ተመራጭ የሆነ የፖለቲካ መስመርም የሀገሪቱን ፖሊሲዎችንና ዕቅዶችንም የመምራት መብት ይኖረዋል። እርግጥ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ይህን መብት ያገኘው፣ መብቱ ከሞላ ጎደል በሁሉም ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስቶች ውስጥ የሚሰፍር አንቀፅ ስለሆነ ብቻ አይደለም። ይልቁንም እንደኛ ያሉ የመድብለ-ፓርቲ ስርዓት የሚከተሉ ሀገሮች ገዥ ፓርቲዎች ይህን ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ገቢራዊ የሚያደርጉት፤ በፓርላማ አብላጫ ወንበር ስላላቸውና የጠራ መስመር በመከተላቸው ምክንያት በድምፅ ብልጫ ሁሌም ስለሚያሸንፉ ነው።
ይሁንና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ገዥ ፓርቲዎች አብላጫ ወንበር ስላላቸውና ህጋዊ እስከሆነ ድረስ የፈለጉትን ጉዳይ በፓርላማ ማሳለፍ ስለሚችሉ ብቻ ሁሉንም ነገር አይከውኑም። ሀገራችን ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኘው ፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም ይህን አካሄድ በጥብቅ የሚያምንና የሚከተል ነው።
የፓርላማው መድረኮች ካለፉት ስርዓቶች ሲንከባለሉ በመጡ ኋላ ቀር አስተሳሰቦች ምክንያት የሚፈጠሩ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካካቶች ላይ ሰፊና ብቃት ያለው ትግል የሚካሄድባቸው እንዲሁም የስራ አስፈፃሚውን ዝርዝር ዕቅድ የሚገመገሙባቸውና ቁጥጥር የሚደረግባቸው ናቸው። የመድረኮቹ ተዋንያን የሆኑት የህዝብ ወኪሎች እነዚህን ጉዳዮች በመከወን የሀገሪቱን የልማት ዕድገት የማስቀጠል አሊያም አሁን ካለበት ይበልጥ እንዲመነደግ የማድረግ ቁልፍ ህገ-መንግስታዊና ህዝባዊ ኃላፈነት ያለባቸው በመሆኑ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎንም ፓርላማ በህዝብ ይሁንታ የሚገቡት የገዥው ፓርቲ አባላት የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ- ኢኮኖሚ አካሄድ በልማታዊ ኢኮኖሚ እሳቤ መተካት እንዳለበት የሚያምኑ ናቸው። እርግጥ ኪራይ ሰብሳቢነት በሂደት ተንዶ በልማታዊነት ሊተካ የሚችለው አመለካከቱን ውጤታማ በሆነ አኳኋን ሊፋለም የሚችል ልማታዊ አስተሳሰብ እየጎለበተ ሲሄድ ነው።
እዚህ ላይ አሳታፊነትን ስንመለከት በህገ-መንግስታችን አንቀፅ 55 ንዑስ አንቀፅ 4 ላይ በግልፅ እንደተደነገገው፤ የፓርላማው አባላት የመላው ህዝብ ወኪል መሆናቸውን እንረዳለን። የአባላቱ ተገዥነትም ለህገ-መንግስቱ ለህዝቡና ለህሊናቸው ብቻ መሆኑንም ጭምር። የአባላቱን ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮ ከፓርላማው ክንዋኔ ጋር በአጭሩ ስንመለከታቸው፤ አባላቱ በፓርላማ ቆይታቸው ማናቸውንም የስራ አስፈፃሚውን ተግባራት በህገ-መንግስቱ መሰረት ብቻ መከናወናቸውን ይቀፐጣጠራሉ፤ ያረጋግጣሉ። በዚህም የህገ-መንግስቱ መሰረታዊ እምነቶች፣ መብቶችና ድንጋጌዎች ገቢራዊ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን በብቃት ይወጣሉ። ተጠሪነታቸው ለህዝቡ በመሆኑም ህዝቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በጥንቃቄ ማጥናትና ማጣራት ዋነኛ ተግባራቸው ነው።
በመሆኑም የህዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች የትኛዎቹ እንደሆኑ በመለየት አስፈፃሚው አካል ጋር ውይይት እንዲፈጠር ያደርጋሉ። የህዝቡን ፍላጎት ተመርኩዘውም አግባብነት ያላቸው ቅሬታዎችም በምን ዓይነት ሁኔታ መፍትሔ ማግኘት እንዳለባቸው በማመላከት ውጤታማ ተግባራትን ያከናውናሉ። በዚህም የህዝቡን በውሳኔዎችና በቁጥጥር ላይ የሚኖረውን ተሳታፊነት እውን ያደርጋሉ ማለት ነው።
ያም ሆነ ይህ የመልካም አስተዳደር መስፈን በመንግሥትና በህዝብ መካከል ሊኖር የሚችለውን ክፍተት የሚዘጋ እንዲሆን በተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የሚመደቡ አመራሮች ውጤታማና ብቃት ሊኖራቸው እንደሚገባ አያጠያይቅም፡፡ ይህን ተግባርም መንግስት ገቢራዊ ለማድረግ እየጣረ ነው። በዚህም ውጤት ማግኘት ችሏል። እዚህ ላይ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ስር በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት የወሰዳቸውን ርምጃዎች ልብ ይሏል!
ታዲያ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ ሁከት በማንኛውም መልኩ አማራጭ አለመሆኑን እንገነዘባለን። ሁከት የዜጎችን ህይወት ከማጥፋት፣ አካልን ከማጉደል፣ ሀብትና ንብረትን ከማጥፋት በስተቀር በልማታዊ እሴቶቻችን ላይ የሚጨምረው አንዳችም ነገር የለም።
ሁከት የሰላም መንገድን የሚዘጋ ተግባር ነው። ሰላም ከሌለ ደግሞ ስለ ልማትና ሰርቶ ስለማደግ ፈፅሞ ማሰብ አይቻልም። በገዛ ሀገር ውስጥ በጉልበተኞች መገዛትን ያስከትላል። ቀማኞችና ዘራፊዎች እንዲያሻቸው እንዲፈነጩ፣ ከሰላም ጋር ፀበኛ የሆኑ ሃይሎች እንዲበራከቱ ምክንያት ይሆናል። ይህም ዴሞክራሲን ለማምጣት የሚደረገውን ትግል በእንጭጩ እንዲቀር ያደርገዋል። በዚህም የሚፈለገው መልካም አስተዳደር ደብዛው ይጠፋል።
እናም መልካም አስተዳደርን በሁከት ዕውን ማድረግ እንደማይቻል መገንዘብ ይገባል። አዎ! የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ሀገሪቱን በመምራት ላይ በሚገኘው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን አማካኝነት ብቻ ነው። የተጀመሩት ሁለንተናዊ

የልማት ትልሞችን በማፋጠንና ከመንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመስራት መልካም አስተዳደርን ዕውን ማድረግ እንደሚቻል ሊዘነጋ አይገባም።