Monday, 30 March 2015

ስኬታማው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ







 ኢህአዴግ የተከተለው ትክክለኛ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ በግብርናና ገጠር ልማት አንጸባራቂ ስኬቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል!!

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ባለፉት 23 አመታት በኢህአዴግ ትክክለኛ ፖሊሲና ቁርጠኛ አመራር እመርታዊ ስኬቶችና ለውጦች ከተመዘገገበባቸው መስኮች ውስጥ የግብርናና የገጠር ልማት አንዱ ነው፡፡ ያለፉት ስርአቶች በተከተሉት ጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝና የተሳሳተ ፖሊሲ ለአራችን እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችል የነበረውን የግብርና ዘርፍ አምክነውታል፣ የአገራችን ህዝቦችንም ለስቃይና ለሰቆቃ ኑሮ ዳርገዋቸው ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የፊውዳል ስርዓት ማቆጥቆጥን ተከትሎ መሬት በአገራችን ቁልፍ የኢኮኖሚ የፖለቲካ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል። በፊውዳሉ ስርዓት የገዢ መደቦች የፖለቲካ ስልጣናቸውን ተጠቅመው የአርሶ አደሩን መብት ረግጠው ጉልበቱንና ምርቱን በመመዝበር የመከራ ህይወትን ሲገፋ ኖሯል። አርሶ አደሮች ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያመረቱትን ምርት በፊውዳሎች እየተቀሙ የበይ ተመልካች ሆነው ለረጅም ዘመናት ኖረዋል፡፡ የንጉሱ ስርአት እንዲወገድ ካደረጉት የህዝቦች መሰረታዊ ጥያቄዎች ውስጥ የመሬት ላራሹ ጥያቄ አንዱ ነበር፡፡ 
የአገራችንን ህዝቦች የትግል ውጤት በሃይል ቀምቶ በፊውዳሉ ስርዓት እግር የተተካው የደርግ አገዛዝ የመሬት ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄ መሆኑን ስለተረዳ ለይስሙላ “መሬት ላራሹ” ብሎ ቢያውጅም በተጨባጭ የፈፀመው የዚህን ተቃራኒ ነበር። ደርግ የወሰደው ጥገናዊ ለውጥ የህዝቦችን የመብት ጥያቄዎች ሳይመልስ የተካሄደ በመሆኑ ቅርጹንና መልኩን ቀይሮ ጭቆናውን ያስቀጠለ ነበር፡፡ ደርግ የአርሶ አደሩ ጉልበትና ምርት በመበዝበዝ በአንድ በኩል የአርሶ አደሩ አቅም እንዲዳከም በሌላ በኩል የራሱን ወታደራዊ አቅም እንዲጎለብት አቅዶ ሰርቷል። በየአካባቢው የእርሻ ሰብል ግብይት ድርጅቶችን በማቋቋም አርሶ አደሩን ያመረተውን ምርት ኮታና የዋጋ ተመን በማውጣት በርካሽ ዋጋ ለመንግስት እንዲሸጥ፣ ኋላም የራሱን ምርት መልሶ ከመንግስት በውድ ዋጋ እንዲገዛ ግዳጅ ጥሎበት ነበር። በወቅቱ መንግስት ባወጣው የዋጋ ተመንና ኮታ መሰረት ከአርሶ አደሩ የገዛውን ምርት በእጥፍ እያተረፈ ሲሸጠው የነበረ ሲሆን ይህም ስርአቱ ምን ያህል በዝባዥ እንደነበረ ያሳያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ህዝቡ በማያምንባቸው ለጦርነት የሚውል ገንዘብ እንዲያዋጣ ይገደድ ነበር፡፡ በተጨማሪም የፊውዳሉም ሆነ የደርግ ስርዓት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአገራችንን አርሶ አደሮች ህይወት ሊቀይሩ የሚችል ትክክለኛ ፖሊሲና የአመራር ድጋፍ መስጠት የሚችሉም የሚፈልጉም አልነበሩም።

የእነዚህ ችግሮች ድምር ውጤት አርሶ አደሩ ለበርካታ ዓመታት በአስከፊ ችግር ውስጥ እንዲቆይ፣ የግብርናው ዘርፍም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የአመራረት ዘይቤ እንዳይላቀቅ አድርጎታል፡፡  ይህ ያለፉት መንግሥታት የተሳሳተ አቅጣጫ አርሶ አደሩን ብቻ ሳይሆን መላ የአገራችንን ህዝቦች ወደ አዘቅት የከተተ በመሆኑ የረጅም ጊዜ ስልጣኔ ታሪክ ባለቤት የነበረችው ሀገራችን በአስከፊ ድህነት፣ ኋላቀርነትና ድንቁርና ልትማቅቅ ግድ ሆኖባታል። ለዚህም ነው ይህን አስከፊ አገራዊ ገጽታና በህዝቦች ላይ የደረሰ ዘግናኝ በደል ለመቀየር የአገራችን ህዝቦች የትውልዶችን ቅብበሎሽ በጠየቀና ከፍተኛ መስዋዕትነት በተከፈለበት ትግል ስርቶቹን ያስወገዷቸው።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ለረጅም ዘመናት ከኖርንበት ድህነት ለመውጣት ከህዝብ ጉልበትና ከመሬት የተሻለ የልማት ግብዓት ሊኖር እንደማይችል ኢህአዴግ በጥብቅ ያምናል። ኢህአዴግ ይህን ነባራዊ ሀቅ በሚገባ በማጤን በፕሮግራሙ ሰፊውን የአገራችንን አርሶ አደርና አርብቶ አደር ለሚያሳትፈው የግብርናና ገጠር ልማት ዘርፍ አመቺ መደላድል መፍጠር እንደሚገባ አስቀምጧል።
ህገ መንግስታችን የኢትዮጵያን ህዝቦችን ታሪክና ለዘመናት በመሬት ሳቢያ የደረሰባቸውን በደል እንዲሁም  በአገራችን ህዝቦች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ መሬት ያለውን ልዩ ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት መሬት የሚመራበት ፖሊሲ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆን አድርጓል። የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት የባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ሆኖ የአርሶ አደሮችና የአርብቶ አደሮችን የመጠቀም መብት ያረጋገጠ እንዲሆን ህገ መንግስቱ ደንግጓል። አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ለኑሯቸው የሚያስፈልጋቸውን መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው የተከበረ መሆኑም በግልጽ ተደንግጓል። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የመሬት ይዞታቸውን የማልማት፣ የመጠቀም፣  የማከራየትና የማውረስ መብታቸውንም ተጎናጽፈዋል። ህገ መንግስታችን “መሬት የማይሸጥ፣ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው” በማለት መሬት በጣት ለሚቆጠሩ ባለፀጋዎች ብቻ ሳይሆን ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝቦች አስተማማኝና ዘላቂ የሃብት ምንጭ እንዲሆን ያደረገው። ይህ በመሆኑ በአገራችን መሬትን በመቆጣጠር በጫናና በተጽዕኖ ሊመጣ የሚችለው የፀረ ዴሞክራሲያዊነት በር ተዘግቷል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ኢሕአዴግ ያስቀመጠው የኢኮኖሚ ልማት አላማ ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ አገራችንን ከተመጽዋችነት የሚያላቅቅ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማረጋገጥ የዳበረ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ መገንባት ነው፡፡ ማንኛውንም አይነት የኢኮኖሚ ልማት ለማረጋገጥ ካፒታል፣ ሰራተኛ የሰው ሃይል፣ መሬትና እነዚህን በውጤታማነት አቀናጅቶ መጠቀም የሚችል አመራር ያስፈልጋል። በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል የካፒታል እጥረት መኖሩና የካፒታል እጥረቱም በአጭር ጊዜ እንደማይፈታም ግልጽ ነው፡፡ በአንጻሩ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ታታሪ የሰው ኃይልና ለልማት የተመቸ በቂ መሬት አለ። ይህም በመሆኑ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቀውን ኢንዱስትሪን ማእከል ያደረገ ልማት የትም እንደማያደረስን የታወቀ ነበር፡፡ በዚህም ምክኒያት ያለንን ሰፊ የሰው ጉልበትና መሬትን እንዲሁም ውስን ካፒታል በመጠቀም የህዝቡ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል የልማት ስትራቴጂ መከተል የግድ ይል ነበር፡፡ ለዚህም ነው ያለንን አቅም ተጠቅመን አገራችን ከብተና ሊታደግ የሚችል ገጠርንና ግብርና ማእከል ያደረግ ስትራቴጂ በመከተል ልማታችን የጀመርነው፡፡
በ1993 የኢህአዴግ ተሃድሶ ተከትሎ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂያችን ነጥሮ ወጥቶ ተግባራዊ በመደረጉ በአገራችን ለተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ባለፉት 23 አመታት ያደረግነው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በቀደሙት ስርዓቶች የተረጂነትና የኋላቀርነት መገለጫ ተደርጎ ሲወሰድ የነበረው ግብርናችን የአርሶ አደሩን ህይወት ከመቀየር አልፎ በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ውስጥ ትርጉም ያለው ሚና እንዲጫወት አስችሏል። የሰው ጉልበትን በስፋት በማነቃነቅና መሬትን በአግባቡ በመጠቀማችን ሀገራችን 12 ተከታታይ ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች ሲሆን ባለፉት አመታት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደጋችን እንደ ሀገር በምግብ እህል ራሳችንን ችለናል።
የተከተልነው ትክክለኛ ፖሊሲያችን ለህዝባችን የመስራትና የመለወጥ ፍላጎት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ምርታማነታችን ከፍተኛ እድገት እየተመዘገበበት መጓዝ ችሏል። በ1983 ዓ.ም በዋና ዋና ሰብሎች 52 ሚሊየን ኩንታል የነበረውን ዓመታዊ የምርት መጠን ባለፈው አመት 269 ሚሊየን ኩንታል ማድረስ ችለናል። ከዚህ ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመረተው በአነስተኛ የአርሶ አደሩ እርሻ አማካኝነት መሆኑን ሲታሰብ ኢህአዴግ አርሶ አደሩና የግብርናው ዘርፍ የዕድገት ምንጭ እንዲሆን የተከተለውን ፖሊሲ ትክክለኛነት ያረጋግጣል፡፡
የግብርና ምርታችን እያደገ የመጣውን የህዝባችን ቁጥር ከመመገብ አልፎ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የኢኮኖሚ መሪነቱን ይዞ ዘልቋል። አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያው አቅም እንዲፈጥር አድርገናል፡፡ ለዚህም ስኬት ገበያ መር የአመራረት ስልት መከተላችንና ይህንኑ ለማገዝ የሚያስችሉ የባለሙያ፣ የተቀናጀ አመራርና የግብዓት አቅርቦት ማሟላታችን በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በ1994 ዓ.ም 14 ሚሊየን ገደማ የነበረው የተረጂዎች ቁጥር በየዓመቱ እየቀነሰ መጥቶ ባለፈው ዓመት ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ቀንሷል። በቀጣይም የተረጂዎችን ቁጥር ዜሮ ለማድረስ እየተረባረብን እንገኛለን። ይህም ህይወቱ በሚሰፈርለት እርዳታ ላይ ተመሰረቶ የነበረውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን ድርቅ በተከሰተ ቁጥር የበርካታ ዜጎች ህይወት ሲቀጠፍበት የነበረውን ሁኔታ በማስቀረት ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበበት ነው፡፡  በ1988 .ም በገጠር ከሚኖረው ህዝብ 47 ነጥብ 5 በመቶው በድህነት ውስጥ ይኖር የነበረ ሲሆን የድህነትን ተራራ ለመናድ ባደረግነው ርብርብ ሀገራዊ የድህነት መጠኑ በ2005 .ም ወደ 26 በመቶ ወርዷል፡፡ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ደግሞ ቁጥሩ ወደ 22 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚወርድ ይጠበቃል።
ቀድሞ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ዘይቤ ውስጥ የነበሩ በርካታ አርሶ አደሮች አሁን ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ወደ መገንባት ተሸጋግረዋል። በአለባበስ፣ በአመጋገብና በአኗኗር ለውጥ አምጥተዋል። ተንቀሳቃሽና መደበኛ ስልክ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል፣ መገናኛ ብዙሃን መጠቀም ጀምረዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት ማፍራት የጀመሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችም በየአካባቢው ተፈጥረዋል። ባፈሩት ሃብት በተለያዩ መስኮች የሚሳተፉ ኢንቨስተሮች ለመሆን በቅተዋል።
ግብርናው በሚያመነጨው ሃብትና ጥሬ ዕቃ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች በፍጥነት እያደጉ ናቸው። ኢኮኖሚያችን ገና ታዳጊ ቢሆንም በእነዚህ ድምር ውጤት ከአንዳንድ የበለጸጉ አገሮች በተሻለ ሁኔታ የሥራ አጥነትን ችግር ተቋቁመን በህዳሴ ጉዞ ወደፊት መገስገስ ቀጥለናል። የመሬት ፖሊሲያችን ለዘመናት የምንታወቅበት የረሃብ ታሪክ እንዲቀየር ከማድረጉም ባሻገር እንደርስበታለን ብለን ባስቀመጥነው ግብ አቅጣጫ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራችን ሽግግር መሰረት እየጣለ ነው።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ኢህአዴግ የተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎች ተጨባጭ ስኬት ማስመዝገብ የቻሉት የአገራችን ህዝቦች ራሳቸው በባለቤትነት የሚያሳተፉበትና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡበት በመሆናቸው ነው። ኢሕአዴግ ከህዝባዊ ባህሪው በመነጨ የኒዮ ሊብራል ሃይሉንና የአገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢ ወኪል የሆኑትን ተላላኪዎቻቸውን ጫና በመመከት ነው። የእነዚህ ሃይሎች ወኪል የሆኑት የአገራችን ተቃዋሚዎችም በተጨባጭ የመጣን ለውጥና እድገት ሸምጥጠው በመካድ እርስ በእርሳቸው የሚምታቱ መሰረተ ቢስ የጭፍን ጥላቻ ሃሳቦችን ሲያቀርቡ ይታያሉ። በአንድ በኩል አርሶ አደሩ መሬቱን ገንዘብ ላላቸው ሃብታሞች እንዳይሸጥ በመከልከል መብቱን ገደባችሁት በማለት ተቆርቋሪ መስለው ሊቀርቡ ይሞክራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መሬት ለባለሃብት እየተሸጠነው ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ከዚህ እርስ በእርሱ ከሚምታታ አቋማቸው መረዳት የሚቻለውም አማራጫቸው ባለፉት ስርቶች ተግባራዊ ሆኖ የወደቀው አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን በጥቂቶች የጭቆና ቀንበር እንዲጫንበት የሚያደርግ ስርዓትን የሚመልስ መሆኑን ነው፡፡     
በአገራችን መሬት በመንግስትና በህዝቡ እጅ ሆኖ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ  የመሬት ፖሊሲ መከተላችን ለአጠቃላይ ልማታችን ያለው ጠቀሜታ በተጨባጭ ተረጋግጧል፡፡ በኒዮ ሊብራል ጫና መሬትን በነፃ ገበያ ሰበብ እንደተራ ሸቀጥ እንዲሸጥ ያደረጉ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮችና ሌሎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ልማት ለማምጣት እንደ አንድ እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ በእንደነዚህ አይነት አገሮች መሬት በተለያየ አጋጣሚ በግለሰቦችና ቡድኖች እጅ በመግባቱ አገሮች የምርት ክንውንንም ሆነ የመንገድ መሠረተ ልማትን የማስፋፋት፣ ለዜጎች የመኖሪያ ቤትና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ገንብቶ ህዝባቸውን ተጠቃሚ የማድረግ ፍላጎታቸውን መወጣት አልቻሉም። መሬትን ለባለፀጎች ሃብት ማካበቻ እንዲሆን አሳልፈው በመስጠታቸው ወደ ኋላ ተመልሶ መሬትን ለህዝቦቻቸው ልማት የማዋሉን ጉዳይ የማይሞክሩት እየሆነባቸው ይገኛል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ኢህአዴግ የነደፋቸውና ተግባር ላይ ያዋላቸው እነዚሁ የትክክለኛ የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፎች ከገባንበት የድህነት አዙሪት ሰብረን እንድንወጣ፣ የአገራችንን ህዝቦች የድህነትና የተረጂነት መጠንን እንድንቀንስ እንዲሁም በከፍተኛ የእድገት ጎዳና እንድንራመድ አስችለውናል፡፡ በአሁኑ ወቅት አገራችን ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከእርዳታ ወደ ትብብር ማዕቀፍና አብሮ በመልማት ላይ ያተኮረም ሆኗል። ለዚህም ግብርናችን ከፍተኛና ወሳኝ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
የግብርናና ገጠር ልማት ስራችን ለዘመናት ተረስቶ በነበረው አርብቶ አደሩም ህይወት ላይ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ያደረገው ኢህአዴግ ነው። ኢህአዴግ ለዘመናት ተገልለውና ተረስተው የቆዩ የአርብቶ አደር አካባቢዎችን የመሠረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ፍትሃዊ ልማትን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። የአርብቶ አደሮቻችን ዋነኛ ማነቆ የሆነውን የውሃ አቅርቦት ችግር መቅረፍ በመጀመራችን አርብቶ አደሩ ተረጋግቶ ለመኖር የሚያስችለው ሁኔታ መፈጠር ጀምሯል። በመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሞቻችን አርብቶ አደሮች አንድ ላይ ተረጋግተው እንዲኖሩና ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲቀየሩም ያደረገ ነው።
በገጠሩ አርሶ አደርም ሆነ አርብቶ አደር ህዝባችን ህይወት ላይ የመጡ ለውጦች የትክክለኛው ግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲያችን ስኬቶች ማሳያ ናቸው። በዚህ ሂደት ያስመዘገብነው እድገትና የጀመርነው የህዳሴ ጉዞ ሊሳካ የሚችለው የፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፎቻችንን ጠብቀን በመጓዝ ለውጤታማነቱ በስፋት ስንንቀሳቀስ ነው። ኢህአዴግ እንደ እስካሁኑ ሁሉ በግብርናና ገጠር ልማት ስራዎቻችን የገጠሩ ብቻ ሳይሆን የከተሜውም ተጠቃሚነት መረጋገጥ እንዲችል ለስኬት ያበቁንን የፖሊሲና ህዝብን ያሳተፉ የልማት ፕሮግራሞች ጠብቆ በመጓዝ የአገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ ይሰራል።
ኢህአዴግን በመምረጥ የህዝብ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ የሚገኘውን ፈጣንና ተከታታይ ልማት እናስቀጥል!!

Friday, 27 March 2015

ታላቁ መሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ በ2002 ምርጫ ማግስት ድምፃችን ይከበር ብሎ በነቂስ ወጥቶ በመስቀል አደባባይ ለተሰበሰበው ህዝብ ካደረጉት አይረሴ ንግግር፡-




እኛ ኢህአዴጎች ህዘቡ በነጻ ሞክራሲ ውሳኔው ለሰጠን ይሁንታ እጅግ እናመሰግናለን ፡፡ የአገራችን ሴቶች መቼም ቢሆን የድርጅታችን የጀርባ አጥንት በመሆን እስካሁን ባገኙት የእኩልነት መብት ላይ በመመስረት ለላቀ ውጤት ለመታገል በድምጻቸው መወሰናቸውን በእጅጉ አናደንቃለን ፤እናመሰግናለም፡፡
የአገራችን ወጣቶች ባለፉት አመታት በተገኘው ልማት ተጠቃሚ የሆኑ ብቻ ሳይሆኑ ውጤቱንም ለማጣጣም በስራ ፈላጊነት የሚጠባበቁትን ቢሆኑ የችግራቸው መፍትሄ የድርጅታችን መስመር መሆኑን ተገንዝበው በአስገራሚ ደረጃ ይሁኝታቸውን ስለሰጡን በእጅጉ እናመሰግናለን፤እንኮራባቸውማለን፡፡
በምርጫው አመትም ቢሆን አማራጭ የሌለውን የመንግስት ግብር መክፈል አለባችሁ ብለን አጥብቀን የያዝናቸው ከዛም አልፈን በአንዳንድ የአፈፃፀም ስህተቶቻችን ቅር ያሰኘናቸው ባለሃብቶች ሳይቀሩ ድርጅታችን ከስህተቶቹ የሚማርና ጉድለቶቹን የሚያስተካክል ድርጅት መሆኑን ተገንዝበው ለሰጡን ድምፅና ድጋፍ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
ከሰፊው የከተሞቻችን ህዝብም ባሻገር መላው የአርሶ አደር ህዝባችን እንደ ወትሮው ራሱንና ድርጅታችንን እንደማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች አድርጎ በመቁጠር የማይናወጥ አቋሙን በድጋሚ በምርጫ ካርዱ በማረጋገጡ የሚሰማን ክብርና ድስታ ወሰን የለውም ፡፡

የአዲስ አበባ ህዝብ በማንኛውም ወቅት ለህዝቡ ድምፅ ያለንን ክብርተመልክቶ ቅሬታ የሚፈጥሩበትን ጉድለቶቻችንን ለማረም ያለንን ቁርጠኝነትና ገና በቀጣይ ማስተካከል ያለብን ነገሮች እንደተጠበቁ ሆኖ ያስመዘገብነውን ድልና ውጤት ተገንዝቦ ከአምስት አመት በኋላ ብይኑን እንደገና በነፃ ምርጫው ሰጥቶናል፡፡የአዲስ አበባ ህዝብ ድምፁን ሲነፍገንም ሆነ ድምፁን ሲሰጠን ከመብትና ጥቅሙ በመነሳት እጅግ ፍትሃዊ የሆነ ብይን የሚሰጥ ህዝብ እንደሆነ በተግባር አረጋግጧል፡፡የመጨረሻውና ፍትሃዊ ዳኛ ለሆነው ህዝባችን ያለንን ክብርና ምስጋና በድጋሚ ለመግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
በዘንድሮው ምርጫ የአዲስ አበባ ህዝብና በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ህዝብ ለኢህአዴግ ጥረትና የስራ ውጤት እውቅና ከመስጠት አልፎ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የማያሻማ መልእክት አስተላልፏል ብዪ አምናለሁ፡፡ህዝብን ለማገልገል የሚያስችል ራእይ ይዞ ከመንቀሳቀስ ይልቅ የጭፍን ጥላቻ ፖለቲካን ማስተናገድ እንደማይፈልግ፤የህዝብ ጥቅምን ሳይሆን የቂም በቀልና ቁርሾ አላማን የሚያራምድ ፖለቲካን ማየት እንደማይፈልግ፤ከሁሉም በላይ ደግሞ በምርጫ ሽፋን የአንድ ሰው ህይወትም ቢሆን መክፈል እንደማይፈልግ በውል አቋሙን ገልጿል ብዪ አምናለሁ፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከድርጅታችን ልምድ ሊወስዱት የሚገባ ትምህርት ያለ ይመስለኛል፡፡የህዝቡን ብይን ሰበብ አስባብ ሳይፈልጉ በፀጋ ሊቀበሉ፤ህዝብ ያልወደደላቸው ነገር ምን እንደሆነ በሰከነ አእምሮ አጢነው ለማስተካከል ቆርጠው ቢነሱ ህዝቡ ፍትሃዊ ዳኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስመስክሯልና በሚቀጥለው ጊዜ ውጤታቸውን አይቶ ሊክሳቸው እንደሚችል ሊገነዘቡ ይገባል እላለሁ፡፡እናም እስካሁን ድረስ ይህንኑ ገንቢ አቅጣጫ ለመከተል ለወሰኑት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለኝን አድናቆት እየገለፅኩ ሌሎቹም ይህንን ፈለግ እንዲከተሉ በህዝቡ ስም እጠይቃለሁ፡፡በከፊል መገለፅ በጀመረው የምርጫ ውጤት እንደታየው ህዝቡ ድምፅ እንደነፈጋቸው በፀጋ በመቀበል የዚህን ኩሩ ህዝብ ብይን ከቶውንም ተፈፃሚነት በማይኖረው የውጭ ሃይሎች ይግባኝ ሰሚነት ለመሸርሸር ከመሞከር እንዲቆጠቡና ለራሳቸውና ለህዝባቸው ውሳኔ ተገቢውን ክብር እንዲሰጡ አሳስባለሁ፡፡
እስካሁን ድረስ በነበረው ሂደት አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ከማናችንም የተሰወረ አይደለም፡፡በምርጫው እለት ታዛቢ ተወካዮቻቸው

ባለፈው ምርጫ ምርጫችንን በመታዘብ ከወገንተኝነት ነፃ ሆነው እንዲመሰክሩ እምነታችንን የጣልንባቸው ታዛቢዎች ወገን ለይተው ሊፋለሙና በእሳት ላይ ነዳጅ ሲያርከፈክፉ በከፍተኛ ቁጭት ተመልክተናል ፡፡ ወዳጅና አጋር እንዲሆኑን የተመኘናቸው አንጋሽ መሆን ሲከጅላቸው ፣የኢትዮጵያ ፖለቲካ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት መሆን ሲቃጣቸው በከፍተኛ ሃዘን ተመልክተናል ፡፡ አሁንም ያለፈው አልፏል ፡፡ በዚህ ኩሩ ህዝብ የወዳጅነትና አጋርነት እጆች አሁንም እንደተዘረጀጉ ናቸው ፡፡ የህዝቡን መሪዎቹን የመምረጥ ሉዓላዊ ስልጣን አክብሩ ፣ ለህዝቡ ውሳኔና ድምፅ ተገቢውን ክብር ስጡ እንላለን ፡፡
የተከበራችሁ የሰላምና የዴሞክራሲ ሰልፈኞች !   
በዘነድሮው ምርጫ ህዝባችን እስካሁን ከተገለፀው ጊዜያዊ ውጤት በመነሳት ይሁንታን እንደሰጠን ግልፅ ቢሆንም ይሁንታቸውን ያልሰጡን ዜጎቻችን እንዳሉም እንገነዘባለን ፡፡ የመረጠንን ህዝብ ድምፅና ውሳኔ እንደምናከብር ሁሉ ያልመረጠንን ህዝብ ድምፅም እንደምናከብር ያለአንዳች ማወላወል ለመግለፅ እወዳለሁ ፡፡ እናም ይሁንታችሁን ያልሰጣችሁንን ዜጎች ቅር ያሰኘንበትን ምክንያት አጥንተን ለማስተካከል እንደምንረባረብ ፣ በሚቀጥለው ጊዜ ይሁንታችሁን ለማግኘት ሌት ተቀን እንደምንጣጣር እስከዚያው ድረስ ደግሞ የምናቋቁመው መንግስት የመረጠንን ህዝብ ብቻ ሳይሆን እናንተንም በእኩልነት እንደሚያገለግል በድርጅታችን መላ አባላትና ሰማዕታት ስም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ፡፡
ምንም አንኳ ህዝባዊ አላማችንና የተደራጀ ርብርባችን ባስገኘልን ታላቅ ህዝባዊ ድጋፍ የምንኮራና የምንደሰት ብንሆንም ህዝቡ እጅግ ከባድ ሃላፊነት በላያችን ላይ እንደጫነም በሚገባ እንገነዘባለን ፡፡ ምንም አንኳ በጥረታችንና በውጤታችን ህዝባችንን በማርካታችን ብንደሰትም አሁንም ህዝባችንን ቅር የሚያሰኙ በርካታ መሰረታዊ ጉድለቶች እንዳሉብን በጥልቀት እንገነዘባለን ፡፡ ስለሆነም በዛሬው የዴሞክራሲ ፌሽታ እለት እኛ ኢህአዴጎች ድምጽ ለሰጠንም ሆነ ላልሰጠን ፍትሃዊ ዳኛ ህዝባችን ያለንን ጥልቅ አክብሮትና ምስጋና በድጋሚ ከልብ እንገልፃለን ፡፡
ምንም እንኳ የምርጫውን ውጤት ሙሉ በሙሉ ከማወቃችን በፊትም ቢሆን በሚቀጥሉት አምስት አመታት የህዝባችንን ፍላጎት ያረካሉ ብለን የቀየስናቸው አቅጣጫዎችና እቅዶች ያሉን ቢሆንም ያገኘነውን እጅት ሰፊ የህዝብ አደራ ታሳቢ በማድረግ እነዚህን እቅዶች ለመተግበር ከመረባረብ ጎን ለጎን የሰጣችሁንን ከፍተኛ ሃላፊነት በይበልጥ መለወጣት ከነገው እለት ጀምሮ እቅዶቻችንን በዝረዝር ፈትሸን መከለስ እነደምንጀምር ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ ፡፡በዚህ አጋጣሚ ያገኘነው ከግምታችን በእጅጉ የላቀ ውጤት ተጨማሪ ከባድ ሸክም ያሸክመን እንደሆነ እንጂ እንደማያኩራራን እንደገና ላረጋጥጥላችኑ እፈልጋለሁ ፡፡
 በምርጫው ያልተሳካላችሁ ተቃዋሚዎች ሁሉ የህዝቡን ድምፅና ውሳኔ ተቀብላችሁ የአገሪቱን ህገ-መንግስትና ህጎች አክብራችሁ እስከተንቀሳቀሳችሁ ድረስ የምክር ቤት ወንበር ቢኖራችሁም ባይኖራችሁም በሁሉም ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች እናንተን ለማማከርና ለማሳተፍ ቃል እንገባላኋላን፡፡ይህን ቃል የምንገባላችሁ በአገራችን የተሃድሶ ትግል አጋር መሆን እደምትችሉና እንደሚገባችሁ ስለምናምን ብቻ ሳይሆን ፣ ምንም ያህል ቁጥር ይኑራቸው ድምፃቸውን ለእናንተው የሰጡ ዜጎች በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍና የመደመጥ መብት እነዳላቸው ጠንቅቀን ስለምናውቅ ጭምር ነው ፡፡ በዛሬው ምርጫ አሸናፊው ይህኛው ወይም ያኛው ድርጅት ሳይሆን አሸናፊው የኢትዮጵያ ህዳሴ ፣አሸናፊው የኢትዮጰያ ዴሞክራሲና የኢትዮጵያ ህዝቦች በመሆናቸው ድሉ የሁላችንም ነው፡፡በመሆኑም ለመላው መራጭ ህዝባችንና የአገራችን የሰላምና የዴሞክራሲ ሃይሎች ከልባችን እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን ፡፡
በድጋሚ በሉዓላዊው የመሾምና የመሻር ስልጣናችሁ ፊት ከአምስት ሚሊዮን በላይ የምንሆን የኢህአዴግ አባላትና ሰማዕታት በታላቅ ትህትና ምስጋናችንን እንገልፃለን ፡፡ እጅ እንነሳለን

Thursday, 26 March 2015

ፌዴራላዊ ስርዓታችን በህዳሴ ጉዞ እንድንገሰግስ አስችሎናል!



የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!

ሀገራችን ኢትዮጵያ የየራሳቸው ቋንቋ፣ ባህል፣ ስነልቦናና መልክዓ ምድራዊ አሰፋፈር ያላቸው ከ75 በላይ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የኃይማኖት ብዝሃነት ያለባት ሀገር ናት። ይሁንና ያለፉት ስርአቶች ብዝሃነትን የሚያስተናግዱ ባለመሆናቸው ሀገራችንና ህዝቦቿን ለአስከፊ ችግሮች ዳርገዋቸው ነበር፡፡ በቅድመ ፌዴራሊዝም የነበሩት መንግስታት በኃይማኖትም ይሁን በቋንቋና ባህል የሚገለፁ ብዝሃነቶችን እንደ ስጋት ይቆጥሩ የነበሩ በመሆናቸው የማንነት ጥያቄዎችን በማፈንና በኃይል ለማጥፋት በህዝቦች ላይ ከፍተኛ ጭቆና አድርሰዋል። የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ገፍፈው ከባርነት ያልተናነሰ ጭቆና አድርሰውባቸዋል።

ሀገራችን ለረጅም ዘመናት ብዝሃነትን ያከበረ ስርዓት መመስረት ባለመቻሏ ገናና የስልጣኔ ታሪኳ በእርስ በእርስ የመሳፍንቶች ሽኩቻና በህዝቦች ላይ በደረሰ የአምባገነኖች ጭፍጨፋ ሊወድም ችሏል። በዚህም የከፍታ ዘመኗ አብቅቶ ታታሪ የነበሩ ህዝቦቿ አሳፋሪ የድህነት፣ የተመፅዋችነትና የጉስቁልና ኑሮ ውስጥ ለመግባት ተገደው እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ገዥዎች የሀገራችን ዋነኛ መገለጫ የሆነውን ብዝሃነትን በመጨፍለቅና በማፈን ላይ የተመሰረተ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ኃይማኖት የሚል አሃዳዊ የመንግስት ስርዓት በመፍጠር በህዝቦች ላይ አስከፊ ጭቆናና በደል አድርሰዋል፡፡ ገዥዎቹ ለወጡበት ብሔርም ጭምር ከሌሎች ህዝቦች ባልተለየ መልኩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆናዎች አድርሰዋል። የሀገራችን ህዝቦች ግን ብዝሃነትን ያልተቀበሉትንና ጭቆናና ግፍ ያደረሱባቸውን ገዥዎች አሜን ብለው ሳይቀበሉ ታግለዋቸዋል፡፡ የሀገራችን አርሶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ተማሪዎች፣ ምሁራንና ሌሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ጊዚያት ገዥዎችን በመታገል መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ ይሁንና በኢህአዴግ እና አባል ድርጅቶቹ ትክክለኛ የትግል መስመር ከመመራታቸው በፊት የነበሩ ትግሎች በአግባቡ የተደራጁና በመሪ ድርጅት ያልታገዙ ስለነበር ገዥዎችን ሊያስወግዱ አልቻሉም፡፡    


ኢህአዴግ ህዝባዊ አላማን በማንገብ የህዝቦችን ትግል በጽናት መርቶና ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎ የዘመናት የህዝቦች ሰቆቃና ስቃይ ምንጭ የነበረውን ብዝሃነትን የማያከብር አምባገነናዊ ስርአት ከህዝቦች ጫንቃ እንዲወገድ አድርጓል፡፡ በኢህአዴግ መሪነት የተካሄደው ትግልም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብቶች ያለ ገደብ የተከበሩባት ኢትዮጵያ ለመፍጠር ሊተመን የማይችል መስዋዕትነት የጠየቀ መሆኑ ወዳጅም ጠላትም የሚገነዘበው ነው። በኢህአዴግ መሪነት በተካሄደው ትግል በአፍሪካ ወደር ያልነበረውን የጦር ሰራዊት የያዘ የጭቆና አገዛዝ ማፈራረስ የተቻለው የትግሉ አላማ ግፍና ጭቆናን የማስወገድ ህዝባዊ ስለነበረ ነው፡፡ በወቅቱ እጅግ ወደተካረረ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረው የብሄር ቅራኔ ሀገርን የመበታተን አደጋ ሳያስከትል የህዝቦችን የበላይነት ባረጋገጠ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲቋጭ ኢህአዴግ ወሳኝ የመሪነት ሚና ተጫውቷል።

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!

የአምባገነናዊ ስርአት መወገድን ተከትሎ የሀገራችን ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ ሊፈታ የሚችል ስርአት መከተል የግድ ይል ነበር፡፡ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ብዝሃነትን በኃይል የመጫን አማራጭ የጥፋት መንገድ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ ስለነበር ብዝሃነትን የሚያከብር አማራጭ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነበር፡፡ የአሃዳዊና የተማከለ የመንግስት አወቃቀር የhገራችን ብዝሃነት የማያስተናግድ መሆኑም ባለፉት መንግስታት በተጨባጭ የታየ ስለነበር የቁልፍ ችግራችን መፍቻ አማራጭ አልነበረም፡፡ የሀገራችን ህዝቦች ከግዳጅ አንድነት ወጥተው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው የተከበረባት ዴሞክራሲያዊ አንድነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመመስረት ለብዝሃነታችን እውቅና የሰጠና ይህንኑ የሚያከብር ፌዴራላዊ ስርዓት መመስረት ወሳኝ ነበር።  በመሆኑም ሁሉም ህዝቦች ወደውና ፈቅደው የሚኖሩበትን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በህገ መንግስታቸው አፅንተዋል።

የፌዴራሊዝም ስርዓት በብዙ ሀገሮች የተለመደ ነው። ከአለም ህዝብ 40 በመቶው የሚይዙ ሀገራት የፌዴራሊዝም ስርዓት ይከተላሉ። በጣም ሰፊ ግዛት ወይም ህዝብ ያለቸው ዴሞክራሲያው ሀገራት ከሞላ ጎደል የሚከተሉት የፌደራል ስርዓትን ነው፡፡ ህንድ፣ ካናዳ፣ ብሪታንያና አሜሪካ የፌደራል ስርዓት ከሚከተሉ ሀገሮች ተጠቃሾች ናቸው።

የእኛን የፌዴራሊዝም ስርዓት ከሌሎቹ የሚለዩት የራሱ ባህሪዎች ግን አሉት። ከእነዚሁ ባህሪያቱ በተለይ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራስ እድል በራስ የመወሰን መብት ለማስከበር ያለው ቁርጠኛ አቋም አንዱ ነው። የእኛ ፌዴራሊዝም ለህዝቦች ማንነት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው። ይህ የማይዋጥላቸው ያለፈው ስርዓት ናፋቂዎች የሆኑት ትምክህተኞች የፌደራል ስርዓቱ ከጅምሩ ሀገር ይበታትናል በሚል አሃዳዊ አገዛዙ እንዲቀጥል ያላደረጉት ጥረት የለም፡፡ በሌላ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነትና የስግብግብነት ፍላጎታቸውን ለማርካት ዝግጁ የሆኑ ጠባብ ኃይሎች በህዝቦች ትግል ተንኮታኩቶ የወደቀ ስርዓት ሲፈጥራቸው የነበሩ ችግሮች አሁንም የቀጠሉ በማስመሰል የህዝቦችን መብት ከሃዲዱ ወጥቶ ለቅራኔና ቁርሾ እንዲውል ጥረት አድርገዋል፡፡ የትምክህት ኃይሉና የጠባብ ኃይሉ የፌደራል ስርዓታችን መበታተንን ሳይሆን ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እየፈጠረ መሆኑ በተረጋገጠበት በአሁኑ ጊዜም የማስመሰያ ጭምብላቸውን እየቀያየሩ በስርዓቱ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ያንፀባርቃሉ፡፡

የትምክህት አመለካከት ወኪል ሆነው የሚንቀሳቀሱ የሀገራችን የተቃዋሚ ፓርቲዎች  ደግሞ በህዝቦች ትግል የተናደውን የግዳጅ አንድነት በመናፈቅ የፌዴራል ስርዓቱን በታኝና ሀገር አጥፊ ነው በማለት በሀሰት ሲተቹና ሲያጣጥሉ ቆይተዋል። የጠባብነት አመለካከት ወኪል ተቃዋሚዎችም ባለፉት ስርዓቶች የነበሩ ችግሮቸ እንዳሉ በማስመሰል የፌደራል ስርዓቱ ላይ ሲዘምቱ ይታያሉ፡፡ ላለፉት 23 ዓመታት በሀገራችን የታየው እውነታ ግን የሀገራችን ተቀዋሚዎች፣ ብዝሃነትን የተቀበለው የፌደራል ስርዓታችን የህዝቦችን የራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንዳስቻላቸው ነው። ዛሬ የሀገራችን ህዝቦች ህገ መንግስታዊ የፌደራል ስርዓታቸው መብቶቻቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ ያረጋገጠላቸው መሆኑን አምነው እጅ ለእጅ ተያይዘው የጋራ ፕሮጀክታቸው የሆነውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ለማሳካት በመረባረብ ላይ ናቸው፡፡

ህገ መንግስታዊ የፌዴራላዊ ስርዓታችን አጠቃላይ ዓላማ የህዝቦችን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ የማስፈን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትን የሚያፋጥን አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ መገንባት ነው። ፌዴራላዊ ስርዓታችን የዜጎች ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዲከበሩ አድርጓል። በህገ መንግስቱ በተደነገጉ አንቀፆች የህግ የበላይነት በማንም ሊጣስ እንደማይችል በግልፅ በማስቀመጥ የዜጎች ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ መብቱን የሚጥስ ማንኛውም አካልም በህግ እንዲጠየቅ የሚያደርግ አሰራር ፈጥሯል። ይህም ህገ መንግስትን በማክበር፣ በማስከበርና ለህጉ ተገዥ በመሆን እንዲፈፀም አድርጓል። የክልሎችና ብሔር ብሔረሰቦች ጥቅሞችን ከማረጋገጥ አኳያም በህገ መንግስታችን አንቀፅ 89 ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሀገሪቷ የተጠራቀመ እውቀትና ሀብት ተጠቃሚ የሚሆኑበት፣ ሀብት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የሚከፋፈልበት እንዲሁም ወደ ኋላ ለቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መንግስት ልዩ ድጋፍ የሚያደርግበት አሰራር እንዲዘረጋ ደንግጓል። ከዚህ አኳያ በተሰሩ ስራዎች ክልሎች የመልማት እድል አግኝተው አቅማቸው እያደገተ በህዝቦቻቸው ኑሮ ላይ የተሻለ ለውጥ እያመጡ መጓዝ ችለዋል። የሀገራችን ፌዴራሊዝም በፉክክር ላይ ሳይሆን በትብብር ላይ የተመሰረተ አብሮ የመልማትና የማደግ አቅጣጫን የሚከተል በመሆኑ የህዝቦችን እኩል የመጠቀም መብት እያረጋገጠ ይገኛል። በትብብር ላይ የተመሰረተ መሆኑ በህዝቦች ሁለንተናዊ እድገት የተገኘውን ስኬት ከፍ እንዲል አድርጎታል።

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፣

ፌዴራላዊ ስርዓታችን ለህዝቦች እኩልነት፣ ፍትሃዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት የሰጠ ነው። አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ጉዞ ያለ ፖለቲካዊ ተሳትፎና እኩልነት ስለማይረጋገጥ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በእኩል የሚያከብር ስርዓት እንዲመሰረት አስችሏል። ፌዴራላዊ ስርዓታችን እነዚህ አጠቃላይ መብቶች እንዲከበሩ በማድረጉ በሀገራችን ላለፉት 23 ዓመታት አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ተችሏል። ለሰላም እጦትና አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት መንስኤ የነበሩ የህዝቦች መብቶች ያለማክበር ችግር በመሰረቱ በመፈታቱ በሀገራችን አስተማማኝ ሰላም ሰፍኗል። በህዝቦች መካከል የሚነሱ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት አማራጭ በማስቀመጡም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መጎልበት ችለዋል።

የፌደራል ስርዓታችን በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ህዝቦች ዋነኛ ጠላታቸው በሆነው ድህነት ላይ እንዲዘምቱ አስችሏቸዋል፡፡ በኢህአዴግ ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመመራትም ፈጣን፣ ተከታታይና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ላይ ናቸው፡፡ ፌዴራላዊ ስርዓታችን የህዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መሰረተ ሰፊ ማህበራዊ ልማትና የመሰረተ ልማት እድገት ያስመዘገበም ነው። አንድ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና የህዝቦችን ትስስር ያጠናከሩ ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ግንባታቸው ተካሂደዋል፡፡ በመካሄድም ላይ ናቸው፡፡

በማህበራዊ ልማት በትምህርትና በጤና ዘርፎች እየተመዘገበ ባለው ውጤት የዜጎች ተጠቃሚነት በእጅጉ ጨምሯል። የፌደራል ስርዓታችን ስኬቶች በድምሩ ሲታዩ ዛሬ የሀገራችን ህዝቦች ተባብረው የሚያድጉበትና አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ገንብተው ታላቅ ህዝብና ሀገር የሚሆኑበት እድል በእጃቸው መሆኑን በተጨባጭ አረጋግጠዋል። ብዝሃነትን ባከበረ ፌዴራላዊ ስርዓት መጓዝ በመቻላቸውም የቀደመውን የሀገራችን ስልጣኔ የማስመለስ ጉዞ ጀምረዋል። ዛሬ የሀገራችን ህዝቦች ከጎረቤት ሀገር ህዝቦች በጋራ የመልማት ተጨባጭ እንቅስቃሴ የጀመሩና ከእራሳቸው ለጎረቤቶቻቸውና ለሌሎች ህዝቦች ሰላም መረጋገጥ እየተጉ ይገኛል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝቦች ልዩነታችን ውበታችን አንድነታችን ጥንካሬያችን በሚለው መርሃቸው እጅ ለእጅ ተያይዘው የጋራ ሀገራቸውን እየገነቡ መገኘታቸው ብዝሃነትን ያከበረ ፌደራላዊ ስርአት የቁልፍ ችግሮቻችን መፍቻ ሁነኛ መሳሪያ እንደሆነ አሳይቷል፡፡

የፌደራል ስርዓታችን ለስኬት የበቃው የሀገራችን ህዝቦች አምነው ስለተቀበሉትና በኢህአዴግ ቁርጠኛ አመራር ሰጭነት በሁሉም መስኮች ተሳትፎአቸው ስለተረጋገጠ ነው፡፡ የፌደራል ስርዓታችን አሁን ከደረሰበት ደረጃ የደረሰው ኢህአዴግ በበሳል ሃሳቦቹ እየመራ በየጊዜው ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ እየሰጠና እራሱን ለቀጣይ ለውጥ እያዘጋጀ በመቀጠሉ ነው፡፡ አሁንም በፈደራል ስርዓታችን የሚታዩ ከማስፈጸም አቅም ውስነት ጋራ የተያያዙ ችግሮች ለመፍታት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል መፍታት እንደሚያስፈልግ ኢህአዴግ ያምናል፡፡ ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የሚነጩ አልፎ አልፎ የህዝቦችን መብቶችን የሚጋፉ ድርጊቶችን ለማረም ኢህአዴግ ከመላ ህዝቡ ጋር በመሆን የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!

ከውድቀታቸው የማይማሩት የድሮ ስርዓት ናፋቂ የሆኑት የሀገራችን ተቃዋሚዎች ዛሬም ከ23 የሰላምና የእድገት ዓመታት በኋላ የፌደራል ስርዓቱ የህዝቦችን መብት ማክበሩ ሀገር ይበትናል የሚለውን መሰረተ ቢስ ውንጀላቸውን አላቆሙም፡፡ የሀገራችን ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያ ህዝቦች ሀቀኛ ትግል በተግባር በውጤት እያደገና እየጎለመሰ የመጣበትና ኢህአዴግ የታገለለት የህዝቦች የበላይነትና ወሳኝነት የነገሰበት ስርዓት ነው። ብዙ ብሔሮች፣ ብዙ ቋንቋዎች፣ ብዙ ባህሎችና ኃይማኖቶች ያሏቸው የሀገራችን ህዝቦች እነዚህ እሴቶቻቸው በእኩል እንዲከበሩ መጠየቅ ቀርቶ መብቶቻቸውን ማሰብ የማይችሉበትን የአምባገነኖች ስርዓት እንዲቀየር ያደረገው ብዝሃነትን ያከበረው ፌዴራላዊ ስርዓታችን መሆኑን ተቃዋሚዎችም ሊክዱት የማይቻላቸው ሀቅ ነው።

የሀገራችን ተቀዋሚዎች ለምትገነቡት ስርዓት ያለችሁ አማራጭ ምንድነው ሲባሉ አንዳንዶቹ በፌደራል ስርዓታችን የመጣውን ለውጥ ፊት ለፊት መካድ ሲከብዳቸው አልሸሹም ዘወር አሉ እንዲሉ ፌደራሊዝምን እንከተላለን ግን አከላለሉን መልክዓ ምድራዊ እናደርገዋለን ይላሉ፡፡ ይህ አማራጭ የህዝቦችን ማንነትና መብት የማይቀበለው ያው ያለፉት አገዛዞች አቋም በፌደራሊዝም አስመሳይ ጭምብል ተሸፍኖ የቀረበ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አማራጭ ብለው የሚያቀርቡት ከየትም ቃርመው የሰበሰቡትን ወክለው የቆሙለትን የትምክህተኞችና የጠባቦችን የተሳሳተና የበሬ ወለደ ወሬን ነው፡፡ ለዚህም ነው የሀገራችን ተቀዋሚዎች አማራጭ ብለው የሚያቀርቡት ሃሳብ ያለፉት ስርዓቶችን መልሶ ለማምጣት ያለመ ለሀገርና ለህዝብ የማይጠቅም የጥፋት መንገድ ነው የምንለው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ባለፉት 23 አመታትም በኢህአዴግ መሪነት መብቶቻቸው ተከብሮ እጅ ለእጅ ተያይዘው ሀገራችንን ወደ ነበረችበት የስልጣኔ ማማ የሚያስወጣ የህዳሴ ጉዞ ጀምረው በስኬት ታጅበው እየተጓዙ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ያበቃቸው ትክክለኛው የኢህአዴግ አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ ወይም ልማትዊ ዴሞክራሲ መስመር መሆኑ የሀገራችን ህዝቦች እንደሚገነዘቡት ኢህአዴግ ያምናል፡፡

ለዚህም ነው የኢህአዴግ መስመር ብቸኛው የህዳሴ መስመር ነው የምንለው፡፡

ለዚህም ነው ኢህአዴግ መምረጥ ፈጣኑንና ቀጣይነት ያለው ልማትን፣ አስተማማኝ ሰላምን እና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲን ማስቀጠል ነው የምንለው፡፡

Wednesday, 25 March 2015

የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ያረጋገጠ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲገነባ በቁርጠኝነት እየታገለ ያለ ህዝባዊ ድርጅት-ኢህአዴግ

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ዋነኛ መገለጫ ህዝቦች የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸው ነው፡፡ ዜጎች በምርጫ ካርዳቸው አማካኝነት ይሁንታቸውን በሰጡት ፓርቲ ብቻ የሚመሩበት ሁኔታ ሲኖር የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እውን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሕዝቡ አንዱን ፓርቲ ከሌሎቹ ፓርቲዎች አስበልጦ እንዲመራው ሃላፊነት መስጠት የሚችለው ደግሞ የተለያዩ አማራጮችን ማቅረብ የሚችሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሲኖሩ ነው፡፡ ስለሆነም በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጮቻቸውን ለህዝብ የሚያቀርቡበት የተመቻቸ ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ 
ከዚህ በተቃራኒ የአንድ ፓርቲ ስርዓት የሚባለው ግን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጫቸው ማቅረብ የማይችሉበትና ህዝቦችም አማራጭ ሐሳብ አግኝተው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ዕድል የማያገኙበት ስርዓት ነው።  እናም የአንድ ፓርቲ ስርዓት የፖለቲካ ልዩነቶች ማስተናገድ የማይችል በመሆኑ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማዕቀፍ ውጭ ነው። በዚህ ስርዓት ውስጥ ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚደራጁበት በምርጫም ተወዳድረው በህዝቡ ይሁንታ የመንግስት ስልጣንን የሚይዙበት አሰራር የተዘጋ ነው።
በሀገራችን ያለፉት ስርዓቶች የህዝቦችን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶችን አፍነው ቆይተዋል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ሕዝቦች እነዚህን ስርዓቶች አሜን ብ ሳይቀበሉ በየጊዜው አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ እየከፈሉ በፅናት ታግለዋቸዋል፡፡ በዚህ የህዝቦች እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችን ሁሉን አቀፍ መስዋዕትነትን የጠየቀውን ትግል በትክለኛ መስመር በመምራት የአንድ ፓርቲ አገዛዙን በማስወገድ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና የብዙሃን ተሳትፎ የተረጋገጠበት የአስተሳሰብ ብዝሃነት እውን እንዲሆን አድርጓል።
በኢህአዴግ መሪነት ለድል የበቃው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ትግል ያረጋገጠው እውነታ ቢኖር ህዝቦች የማያምኑበት ማንኛውም ዓይነት ስርዓት እንዲመራቸው እንደማይፈቅዱና በኃይል ሊገዛቸው ቢፈልግም የኃይል አገዛዙ ዕድሜ እንደማይኖረው ነው፡፡ ኢህአዴግ በህዝባችን ተሳትፎና መስዋእትነት የጨቋኞችና አምባገነኖችን አስተዳደር ከመሰረቱ በመናድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት የሀገራችን ዘላቂ ሰላም ከማረጋገጥ በተጨማሪ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችንም በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲጓዝ አድርጓል። በዚህም የህዝባችን ብቸኛ የስልጣን ምንጭነትና ባለቤትነት ማረጋገጥ ችሏል።
ህገ መንግስታችን ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መሰረት ሆኗል!

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
ኢህአዴግ የህዝቦችን ትግል በግንባር ቀደምነት በመምራት አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ቢያስወግድም ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎ ያገኘውን ስልጣን ለብቻው መያዝን ምርጫው አላደረገም፡፡ ይልቁንም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም እና ሁሉም ሃይሎች በሽግግሩ እንዲሳተፉና የሀገሪቱ መፃኢ እጣ ፈንታ በጋራ የሚወስኑበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥሪ አድርጓል፡፡ የደርግን ስርዓት ለመጣል ከየአቅጣጫው መሳሪያ ያነሱ የተለያዩ የታጠቁ ሃይሎችን ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲዎችን፣ ቡድኖችንና ግለሰቦችን በማካተት በአዲሲቱ ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉበት ሁኔታ ያመቻቸ የሽግግር መንግስት ስርዓት ተዘርግቷል፡፡ ይህምአዴግ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መስፈን መሰረት በመጣል ሂደት  ለነበረው ቁርጠኝነት መገለጫ ነው፡፡
በሽግግር መድረኩ ወቅት ሁሉም ተሳታፊ አካላት ለሀገሪቱ ይበጃል ያሉትን ሃሳብ በማቅረብ ጠቃሚ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ውይይት አድርገዋል፡፡ ይህ ወቅት በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የቻሉ ሃሳቦች ገዢ በመሆን ተግባራዊ እየተደረጉ የሚሄዱበት የመንግስታዊ ስርዓት መሰረት የተጣለበትና አሃዳዊ የነበረው የመንግስት ስርዓት በመሰረቱ መቀየሩ በይፋ የታወጀበትነበር፡፡ በወቅቱ በኢህአዴግ ግንባር ቀደም ተዋናይነት የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን በማዋቀር የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ታሪክ፣ ባህልና እምነት እንዲሁም የሀገራችንን ራዕይ መሰረት ያደረገ ረቂቅ ህገ መንግስት ተዘጋጅቷል፡፡

በሽግግር መንግስቱ ወቅት በተዘጋጀው ረቂቅ ህገ መንግስት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ በተለያየ ደረጃ የሕብረተሰብ ተወካዮችን በማሳተፍ ሰፊ ውይይቶችን ከተደረጉ በኋላ የማሻሻያ ግብዓቶች ታክለውበት የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በስራ ላይ እንዲውል ማድረግም ተችሏል፡፡ በሕገ መንግስቱ ከተካተቱ አዳዲስ አስተሳሰቦችና እምነቶች መካከልም የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ይገኝበታል። ሕገ መንግስታችን ለሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ዋስትና ሰጥቷል ስንልም ከያዛቸው ድንጋጌዎች በመነሳት ነው፡፡ ህገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን በማያሻማ መንገድ በመደንገግ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ዋነኛ መገለጫ የሆነውን የህዝብ ሉዓላዊነት በተግባር አረጋግጧል፡፡ 
ህገ መንግስቱ በአንቀፅ 29 “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላልበማለት ከጅምሩ ልዩነቶች መደፍጠጥ እንደማይገባቸው ይደነግጋል፡፡ ዜጎች ይህን አስተሳሰባቸውን በጋራ በመሆን በተደራጀ መንገድ ለማራመድ ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ በፖለቲካ ፓርቲነት መደራጀት ነው፡፡ ይህም በህገ መንግስቱ ሙሉ እውቅና ያገኘ መብት ነው፡፡ ዜጎች ለተወሰነ አላማ መደራጀት ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፤ የመሰብሰብና አቤቱታ የማቅረብ መብትም አላቸው፡፡ የዜጎች ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የመደራጀት መብት ህገ መንግስታዊ ዋስትና ማግኘቱን ተከትሎ የተለያየ ፖለቲካዊ አቋምን የያዙ በርካታ ሀገራዊና ክልላዊ ፓርቲዎች ተቋቁመው በነፃነት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜም 75 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየደረጃው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ይህም የሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ነው።  
በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር የሚያስፈልገው ሕዝቡ የተለያዩ አማራጮች እየቀረቡለት ከቀረቡ አማራጮች መካከል የሚበጀውን እየመረጠ ለስልጣን የሚያበቃበት ሁኔታ ለመፍጠር በመሆኑ ኢህአዴግ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው በቁርጠኝነት እየሰራ መጥቷል። በኢህአዴግ መሪነት በሀገራችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ህገ መንግስታዊ እውቅና ከማግኘቱም በላይ በተግባርም ሰፊ የግል ህትመትና ኤፍ ኤም ሬዲዮ ሚዲያዎች መስፋፋት በመጀመራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጫቸውን ለህዝብ ማቅረብ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ህገ መንግስታዊ ዋስትና ያላቸው እነዚህ መብቶች በቡድንና በተናጠል የተፈቀዱና ጥበቃም የሚደረግላቸው ሲሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፓርቲ ልሳን ማውጣትና ለአባላቶቻቸው በነፃነት ማሰራጨት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ምርጫዎቻችን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ስኬቶች ናቸው!!
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች፤

የፖለቲካ ፓርቲዎች ግብ የሚሆነው የቀረፁትን ፕሮግራም ለመፈፀም የሚያስችላቸውን መንግስታዊ ስልጣን በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች መያዝ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ አስቀድሞ በተወሰነለት ጊዜ በመደበኛነት የሚካሄድ ምርጫ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም በሀገራችን የሚካሄዱ ምርጫዎችን የሚመራና የሚያስተዳድር ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውግንና ነፃና ገለልተኛ የሆነ ቦርድ በህገ መንግስቱ መሰረት ተቋቋቁሟል፡፡ ቦርዱ ሲቋቋም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጭምር የቦርዱ አባላት የሚሆኑ ዕጩዎችን በማቅረብ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ የምርጫ ህጎቻችንም እንዲሁ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ሰፊ ስራ ተከናውኗል። በተለይ በሶስተኛው ዙር አጠቃላይ ምርጫ ማግስት ከፓርቲዎች ጋር በተደረጉ ሰፊ ውይይትችና ምክክሮች የምርጫ ህጉ እንዲሻሻል በማድረግ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ለማጠናከር በኢህአዴግ ግንባር ቀደም ተዋናይነት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። የቦርዱ አሰራርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና እየተጠናከረ መጥቷል። እናም ቦርዱ በህገ መንግስቱ የተሰጠው ስልጣንና ተግባር በገለልተኝነት እያከናወነ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው። 
ይሁንና ህጋዊና ህገወጥ መንገዶችን እያጣቀሱ መጓዝን የመረጡ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘወትር ቦርዱን በሀሰት መወንጀላቸውን ቀጥለውበታል፡፡ እነዚህ አፍራሽ ኃይሎች ቦርዱን ለማጠልሸት ሌት ተቀን የሚተጉት የራሳቸው ህገ ወጥ ተግባር ለመሸፈን በማሰብ እንደሆነ መላው የሀገራችን ህዝቦች የሚገነዘቡት ጉዳይ ነው።
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 38 ማንኛውም ዜጋ በቀለም፤ በዘር፤ በሃይማኖት ወይም በአመለካከት ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳለው በደነገገው መሰረት እስካሁን በሀገራችን አራት አጠቃላይና አካባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በእነዚህ ምርጫዎች የታየው የህዝብ ተሳትፎም እጅግ ከፍተኛና በእርግጥም የህዝቡን ወሳኝነት በተግባር ያረጋገጠ ነው። ምርጫዎቹ ነፃ፤ ፍትሃዊ፤ ዴሞክራሲያዊና በመላው ህዝብ ተሳትፎ የተፈፀሙ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች መሆናችንን ያረጋገጡ ምርጫዎች ናቸው፡፡
ለአብነት በመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር ምርጫዎች የተወዳደሩ ፓርቲዎች ብዛት እንደቅደም ተከተላቸው 57 እና 49 ሲሆኑ የፓርላማ መቀመጫ ያገኙ ፓርቲዎች ብዛትም እንደቅደምተከተላቸው 43 እና 42 ነበሩ፡፡ 2002ቱን ምርጫም እንዲሁ ከተመዘገቡት 31 ሚልዮን 926ሺህ,520 ሰዎች መካከል 93.4 በመቶ ያክሉ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ተሳትፎው ከሌሎች አገሮች ልምድ ጋር ሲነፃፀርም እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡
በ2002 በተካሄደው ምርጫ 63 የፖለቲካ ፓርቲዎች 2ሺህ 188 ዕጩዎች ለተወካዮች ምክር ቤት፤ 4ሺህ 746 ዕጩዎች ለክልል ምክር ቤቶች እና 45 ዕጩዎች በግል ተወዳድረዋል፡፡ ይህ ለአንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር በአማካይ ከአራት በላይ ዕጩዎች፤ ለአንድ የክልል ምክር ቤት ወንበር ደግሞ በአማካይ ሶስት ተወዳዳሪዎች መቅረባቸውንና ውድድሩ ጠንካራ እንደነበር ያመለክታል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም በምርጫው ሂደቶች ነፃ ሆነው ዘግበዋል፡፡ በመጨረሻም ሕብረተሰቡ ከቀረቡለት አማራጮች ውስጥ የኢህአዴግ መስመር የሀገሪቱን ህዳሴ ማረጋገጥ የሚችል ብቸኛ መስመር መሆኑን በመተማመን  ድምፁን ለኢህአዴግ ሰጥቷል፡፡ ለዚህም ኢህአዴግ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
በቀደሙት ሶስት አጠቃላይ ምርጫዎች ኢህአዴግ በህዝባችን ይሁንታ በአብላጫ ድምፅ እያሸነፈ ከህዝቡ የተሰጠው ከፍተኛ ኃላፊነት በቁርጠኝነትና በከፍተኛ ዲስፕሊን እየተወጣ መጥቷል። በምርጫ 2002 ደግሞ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከምክር ቤቶች የተገለሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ኢህአዴግ ደግሞ በአንፃሩ ከፍተኛ ይሁንታን አግኝቷል። ከህዝቡ የተሰጠው ከፍተኛ ኃላፊነት በመገንዘብም የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ይበልጥ ለማጎልበት የሚያስችሉ ስኬታማ ስራዎች አከናውኗል። ኢህአዴግ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጠናከር በቁርጠኝነት ሲሰራ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ግን ህዝቡን ሊያሳምን የሚችል የፖሊሲ አማራጭ ማቅረብ ባለመቻላቸው የሀገራችን ህዝቦች ይሁንታ በተደጋጋሚ ተነፍገዋል፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ የአውራ ፓርቲ መልክ ይዞ እንዲጓዝ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
የሀገራችን ህዝቦች የሀገሪቱን ህዳሴ እውን ለማድረግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ሌት ተቀን ለሚተጋው ኢህአዴግ ድምፃቸው ሰጥተው ተቃዋሚዎች ግን የሀገራችን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ማረጋገጥ እንደማይችሉ በድምፀቸው ባረጋገጡበት ሁኔታ ተቃዋሚዎች የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ የተቀለበሰ ለማስመሰል ተረባርበዋል፡፡ ህዝቡ ለምን ድምፁን እንዳልሰጣቸው ራሳቸውን በአግባቡ ፈትሸው ለማሻሻል ከመሯሯጥ ይልቅ ኢህአዴግን መኮነን  መርጠዋል። የአውራ ፓርቲ ስርዓትን ከአንድ ፓርቲ ስርዓት ጋር ለማመሳሰልና መሰረተ ቢስ በሆነ ክስ ህዝቡን ለማደናገርም ሞክረዋል፡፡
የአውራ ፓርቲ ስርዓት በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች ተግባራዊ የሆነና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አካል ሆኖ ሳለም ኢህአዴግ ያመጣው እስከማስመሰል ተጣድፈዋል። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት በተሻለ ሁኔታ ተራምደዋል የሚባሉ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ሳይቀር የአውራ ፓርቲ ስርዓት እውን ሆኖባቸዋል። የሲዊድን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፣ የሜክሲኮው ሪቮልሽናል ኢንስቲትሹናል ፓርቲ እንዲሁም የጃፓኑ ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከ40 እስከ 60 ዓመታት በስልጣን የቆዩበት እውነታ እናገኛለን። 
በአህጉራችንም የአውራ ፓርቲ ስርዓት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየና አሁንም ያለ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አንድ አካል ነው፡፡ ለአብነት የታንዛኒያው ቻማ ቻማ፤ የአንጎላው ዘ ፖፑላር ፍሮንት ፎር ሊብሬሽን ኦፍ አንጎላ፤ የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ኮንግረስ ፓርቲ ለበርካታ ጊዜያቶች በተደጋጋሚ በማሸነፍ አገሮቻቸውን እየመሩ ቆይተዋል፡፡ በአውራ ፓርቲ ስርዓት ረጅም ታሪክ ያላት ሌላኛዋ አፍሪካዊት አገር ቦትስዋና ስትሆን የቦትስዋና ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከ1965 ጀምሮ በበርካታ ምርጫዎች በማሸነፍ እስካሁን በስልጣን ላይ ይገኛል፡፡
በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ወሳኙ ጉዳይም የትኛው ፓርቲ ስንት ጊዜ በስልጣን ላይ ቆየ ሳይሆን ህዝቡ በእውን ድምፁን በነፃነት ይሁንታውን ሰጥተዋል ወይ የሚለው ይሆናል። እናም ህዝቡ በነፃነት ወጥቶ ያለምንም ጫናና ተፅዕኖ ድምፁን እስከሰጠና የመንግስታዊ ስልጣን ብቸኛው ምንጭ ህዝቡ እስከሆነ ድረስ የህዝቡ ይሁንታ ያገኘ አካል በተደጋጋሚ መመረጡ ስርዓቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አይደለም ተብሎ ከተቃዋሚዎች የሚነሳው ሐሳብ ውሃ የሚቋጥር አይደለም።  
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
በዴሞክራሲያቸው አደጉ የሚባሉት ሀገራት አሁን ካሉበት የዴሞክራሲ ደረጃ ለመድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ የእኛ ዴሞክራሲ ግን በዕድሜው ለጋ የሚባል ዴሞክራሲ ቢሆንም በእስካሁን ሂደቱ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል። በመድብለ ፓርቲ ስርዓትም ቢሆን በሀገራችን በርካታ ፓርቲዎች በነፃነት የሚሳተፉበትና የህዝቡን የስልጣን ምንጭነትና ተቆጣጣሪነት በተግባር ማረጋገጥ ችለናል። የዴሞክራሲ ባህል የመገንባት ጉዳይ ቀጣይነት ያለው ትግል የሚጠይቅ ሂደት ቢሆንም በእስካሁን ጉዟችን ውጤታማ ስኬቶች አስመዘግብናል። በቀጣይም የዴሞክራሲ ስርዓታችን ይበልጥ መዳበር እንዳለበትና የህዝቦች የዴሞክራሲ ተሳትፎም እየጎለበት መሄድ እንዳለበት ይገነዘባል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢህአዴግ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መጎልበት አሁንም ሃላፊነቱን በቁርጠኘነት መወጣቱን እንደሚቀጥል ለመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዳግም ያረጋግጣል፡፡
ኢህአዴግን መምረጥ፤ ህዝቦች ለዘመናት ተነፍገው የቆዩትንና በኋላም በመራራ ትግላቸው የተጎናጸፉትን የዴሞክራሲ ስርዓት ማጠናከርና ማስቀጠል ነው፡፡
ኢህአዴግ የሚያስተላልፋቸውን የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶች ከቴሌቪዥን፤ ሬዲዮና ጋዜጣ በተጨማሪ