Wednesday, 25 March 2015

የኦህዴድ 25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓልን አስመልክቶ በኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የወጣ መግለጫ

የኦህዴድ 25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓልን አስመልክቶ በኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የወጣ መግለጫ
እንደሚታወቀው ሁሉ መጋቢት 17/1982 ኦህዴድ የተመሰረተበት ታሪካዊ ዕለት በመሆኑ በኦሮሞ ህዝብ የትግል ታሪክ ውስጥ ያለው ትርጉም የላቀ ነው፡፡ የኦህዴድ ምስረታ በዓል በኦሮሞ ህዝብና በጠቅላላ በሀገሪቷ ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ትርጉም በትክክል በመገንዘብ ቀኑን ስናከብር ኦህዴድ እንደ ክልልና እንደ ሀገር ያለውን የአመራር ሚና በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ቁርጠኝነቱን የሚያሳይበት፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ በኦህዴድ/ኢህአዴግ መሪነት የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ትግላችንን ከግቡ ለማድረስ ቃላቸውን የሚያድሱበት ቀን ሆኖ በየዓመቱ ሲከበር የመጣ ሲሆን እነሆ ዛሬ ለ25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓል በቅቷል፡፡
ድርጅታችን ኦህዴድ በትግል፣ በመስዕዋትነትና በድል ያሸበረቀ የ25 ዓመት ዕድሜ የቆጠረ ወጣት ድርጅት ሲሆን፣ የተጀመረውን የዕድገት ጐዳና በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል አስተማማኝ የአመራር ብቃት ያካበተና እየታዩ ያሉትን ለውጦች ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከመቼውም በላይ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
ይህን የኦህዴድ 25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓል የምናከብረው በኦህዴድ/ኢህአዴግ አመራር የተጀመረው የዕድገት ጉዞ በሁሉም መስክ በአስተማማኝ ሁኔታ ቀጣዩን የክልላችንም ሆነ የሀገራችን ውብ ገጽታ በግልጽ እያሳየ የመጣበትና የዕድገቱን ግቦች ወደላቀ ደረጃ የሚያደርሱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የመጀመሪያ ዙር ዕቅዳችንን በብቃት ለማጠናቀቅ ሁሉ አቀፍ እንቅስቃሴ በምናደርግበት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በተጨማሪም በዓሉ የሚከበረው 5ኛውን ዙር አጠቃላይ ምርጫ እንደ ሀገርና እንደ ክልል ለማካሄድ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ባለበትና ድርጅታችን በምርጫው ተወዳድሮ ለማሸነፍ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ የደረሰውን የአመራር ህዳሴ እንቅስቃሴ በማስቀጠልና ከግቡ በማድረስ የህዝቡን አመኔታና ተስፋ አፍርቶ ለምርጫው በቀረበበት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡
ስለዚህ ልዩና ታሪካዊ በሆነ ወቅት ውስጥ የሚከበረው ይህ የ25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓላችን ኦህዴድና ህዝባችን ያለፉትን የ25 ዓመታት የትግልና የድል ጉዞዎች መለስ ብለን የምንቃኝበትና ዛሬ የደረስንበትን ደረጃ በትክክል ተገንዝበን ከምንጊዜውም በላይ ተደራጅተንና ጠንክረን ከፊታችን የሚጠብቁንን ታላላቅ ሥራዎች ለማሳካት ያለንን ቁርጠኝነት መልሰን የምናረጋግጥበት ነው፡፡ እንዲሁም ድርጅታችን በዓሉን ሲያከብር በ25 ዓመት የትግል ጉዞ ውስጥ የኦሮሞን ህዝብ መብት ለማስከበርና ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ የተረጋገጠባት፣ በህዝቦቿ አንድነት ላይ የተመሰረተች አዲስቷን ኢትዩጵያን እውን ለማድረግ በተለያዩ የትግሉ ምዕራፎች ውስጥ ክቡር የህይወት መስዕዋትነት የከፈሉ ታጋዮችን በታላቅ ክብር በማስታወስ አደራቸውን ጠብቆ ከግቡ ለማድረስ ቃሉን ያድሳል፡፡
በዚህ አጋጣሚ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሀገራችንን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም አባላቱና ደጋፊዎቹ፣ የሀገሪቷ የዴሞክራሲ ኃይሎችና የትግል አጋሮቹን በሙሉ እንኳን ለዚህ ታሪካዊ በዓል አደረሳችሁ፤ እንኳን አደረሰን ይላል፡፡
እንደሚታወቀው የዛሬ 25 ዓመት የተወሰኑ የኦሮሞ ታጋዮች የኦሮሞን ህዝብ መብትና ጥቅም ሊያስከብር የሚችል የተቀደሰ ዓላማ ይዘው ኦህዴድን በመመሥረት የወሰዱት ታሪካዊ እርምጃ በኦሮሞ ህዝብ ትግል ሂደት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነበር፡፡
ኦህዴድ የመጀመሪያው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሆኖ በኦሮሞ ህዝብ ትግል ውስጥ መቀላቀሉ ትግሉን በትክክለኛ ስትራቴጂ መርቶ ከግቡ ለማድረስ የሚችል ቆራጥ የፖለቲካ ድርጅት በማጣት ሲንፏቀቅ የነበረውን የህዝባችንን ትግል ትክክለኛ መስመር በማስያዝ፣ በማቀናጀትና አፋጥኖ በማራመድ ለድል ለማብቃት ያበረከተው አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው፡፡
በተለይም በሰሜኑ ኢትዮጵያ በሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የሚካሄደው የፀረ - ጭቆና ትግሉ እየተጠናከረ በመጣ ሰዓት ላይ ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ጋር አስተሳስሮ ለመምራት የሀገራችንን ጭቁን ህዝቦች የትግል ክንድ እጅግ በማጠናከርና የደርግ ሥርዓት ዕድሜ እንዲያጥር የኦሮሞና የመላው ብሔር ብሔረሰቦች መብት የተከበረበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንዲከፈት ወሳኝ ድርሻ ሊወጣ ችሏል፡፡
በአጠቃላይ ያለፉት 25 ዓመታት የድርጅታችን ታሪክ ለሀገራችንና ህዝባችን ጥቅም ክቡር መስዕዋትነት የተከፈለበት፣ በሁሉም አቅጣጫ በተመዘገቡ ድሎች የደመቀ ስኬታማ የትግል ታሪከ ነው፡፡ የ25 ዓመቱ የኦህዴድ ዕድሜ በኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ውስጥ ህዝባችን ለብዙ ዓመታት ሲመኝ የነበረውን ወሳኝ የፖለቲካ ጥያቄዎች መልስ ሊያገኝ የቻለበት፣ የኦሮሞ ህዝብ ሁሉንም መሠረታዊ መብቶች ተጐናጽፎ፣ ኦሮሞነት ክብር ሆኖ፣ የኦሮሞ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ መስፋፋት የጀመረበት፣ ህዝባችን አስተማማኝ ሰላም አግኝቶ በክልሉ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ፣ ዕውቀቱንና ጉልበቱን በማቀናጀት በእልህ ሰርቶ ኑሮውን ማሻሻል የጀመረበትና በሀገሪቷ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እኩል ተጠቃሚና ተሳታፊ መሆን የቻለበት በመሆኑ በኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ውስጥ ደማቅ ምዕራፍ ይዞ የሚኖር ነው፡፡ በዚህ ተግባሩም ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ወደ አዲስና ክቡር ምዕራፍ ያሸጋገረና በማንኛውም የስም አጥፊነት ኘሮፓጋንዳ ሊደበዝዝ የማይችል ህዝባችን በማንኛውም ወቅት የሚኮራበት ታሪክ ያስመዘገበ መሆኑን በተጨባጭ አረጋግጧል፡፡
ዛሬ 25 ዓመታትን መለስ ብለን ስናይ የጭቆናው ዘመናት እየራቁ፣ ከአሰቃቂ ድህነት በየደረጃው እየወጣንና ወደ ከፍተኛ ዕድገት እየቀረብን በስኬት ጐዳና ላይ እየተጓዝን ነን፡፡ ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ዛሬ ባለንበት የስኬት ደረጃ ላይ ያደረሰው በቀላሉ ሳይሆን በየትግሉ ምዕራፍ ያጋጠሙትን ፈተናዎችና ውስብስብ ችግሮች ከህዝቡ ጋር ሆኖ በብርታት በመታገልና ትግሉ የሚጠይቀውን መስዕዋትነት ሁሉ እየከፈለ ወደፊት ሊራመድ በመቻሉ ነው፡፡
ከዚህም አንፃር በጠባብነትና የትምክህተኝነት አመለካከት ተነድተው የጥገኝነት ፍላጐታቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የጥፋት ኃይሎች ኦሮሚያን የሁከት ማዕከል ለማድረግ የሐሰት ኘሮፓጋንዳ በመንዛት፣ በስም ማጥቆርና ኃይል ተጠቅመው በኦህዴድና በህዝቡ መካከል አጥር ለማጠርና ድርጅቱን ለማሰናከል ያደረጉት ጥረት በጣም ከባድ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ዘመቻ በኦህዴድ አመራርና በኦሮሞ ህዝብ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን በአጠቃላይ በሀገሪቱ የሚገነባው አዲስ ሥርዓት በእንጭጩ እንዲፈርስ በማድረግ ላይ ያተኮረ ስለነበር እንደሀገርም በጣም አሳሳቢ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ኦህዴድ ለነዚህ ፀረ- ህዝቦች ጀርባውን ሳይሆን ግንባሩን ሰጥቶ ከፍተኛ መስዕዋትነት በመክፈል በነዚህ የጥፋት ኃይሎች ተወጥኖ የነበረውን አዲሱን ሥርዓት የማፍረስ ደባ ከህዝቡ ጋር ሆኖ በማክሸፍና አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ የከፈለው መስዕዋትነት ድርጅታችን አዲሲቷን ኢትዮጵያ በአስተማማኝና የሰላም መሠረት ላይ ለመገንባት ወሳኝ ሚና የተጫወተ ድርጅት እንዲሆን አድርጐታል፡፡
በዚሁ መሠረት ድርጅታችን ኦህዴድ በአንድ በኩል ከህዝቡ ጋር ሆኖ የፀረ -ሰላም ኃይሎችን ደባ በቀጣይነት እያከሸፈ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የብሔር፣ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት፣ የሴቶች እኩልነት፣ የኃይማኖት እኩልነትና ነፃነት፣ ለሁሉም መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ዋስትና የሆነው የዲሞክራሲያዊ መንግስት ህገ-መንግስት እንዲጸድቅ፤ በዚህም ላይ ተመስርቶ ፌዴራላዊ ሥርዓት እንዲዘረጋና የኦሮሞ ህዝብና መላው የሀገሪቷ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ ለማድረግ የግንባር ቀደምነቱን ድርሻ በመወጣት የፈጸመው አኩሪ ሥራ በታሪክ ውስጥ ምንጊዜም እየተወሳ የሚኖር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኦህዴድ የኦሮሞን ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና ብሔራዊ አመለካከትን በመገንባት በኦሮሚያ ክልልና በሀገር ደረጃም የመቻቻል ባህል፣ መከባበርና በተባበረ ክንድ የጋራ ሀገር ለመገንባት የሚደረገው ርብርብ እንዲጠናከር፣ እንዲሁም ልማታዊ አመለካከትና የሥራ ባህልን በማዳበር ህዝቡ ዋና ጠላቱ በሆነው ድህነት ላይ በተደራጀ መንገድ እየዘመተ፣ ተሳትፎውንና ተጠቃሚነቱን እጅግ እያረጋገጠ ትክክለኛ አቅጣጫ ይዞ እንዲሄድ በመምራት ረገድ የሰራው ሥራና ያስመዘገበው ውጤት የድርጅታችንን ፖለቲካ አመራር ብቃት በላቀ ደረጃ ያረጋገጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በተለይም ድርጅታችን በ1993 ዓ.ም በጀመረው የተሃድሶ እንቅስቃሴ የድርጅቱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር እጅግ ጠርቶ ከወጣና በዕድገቱ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ኘሮግራሞች ተዘርዝሮ ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ ወዲህ ህዝባችን የድርጅታችንን መስመር በሙሉ እምነት ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ በመጀመሩ በቀጣይነት እየታየ ያለው ለውጥ በጣም ፈጣን፣ አስተማማኝና የሀገራችንና የክልላችንን ብሩህ ተስፋ ከወዲሁ የሚያሳይ እየሆነ መጥቷል፡፡
በዚህ ሂደት እየተመዘገበ ያለው ተስፋ ሰጪ የዕድገት ውጤትም የድርጅታችን መስመር የህዝቡን መብትና ጥቅም የሚያስከብር፣ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት የሚያረጋግጥና የሀገራችንን ራዕይ ሊያሳካ የሚችል መስመር መሆኑን በተጨባጭ ሊያሳይ ችሏል፡፡
በአጠቃላይ በድርጅታችን አመራር በክልላችን በድህነት ላይ አምርሮ በመታገል ራሱን፣ ክልሉንና ሀገሩን ለማሳደግ በእልህ የሚሰራ ህብረተሰብ በተጨባጭ ተፈጥሯል፡፡ የድርጅታችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር መላ ህብረተሰቡን ለለውጥ ማነሳሳት በመጀመሩ በጣም ከባድ ሲመስል የነበረው የድህነት ተራራ በህዝቡ ማዕበል ተንገዳግዶ መፍረስ ጀምሯል፡፡ በኦህዴድ አመራር የክልላችን ልማት በሁሉም መስክ አብቦ ህዝባችን ከጣፋጭ ውጤቱ ከመጠቀም አልፎ ለበለጠ ዕድገት በተሟላ ቁርጠኝነትና በእልህ መንቀሳቀስ የጀመረበት ሁኔታም በተጨባጭ እየታየ መጥቷል፡፡ ፈጣን፣ መሠረተ ሰፊና መላው ህዝብ ደረጃ በደረጃ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ልማት በህዝቡ ሁለንተናዊ ርብርብ ለማረጋገጥ በዕቅድና በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ ባለው ሥራ ለረዥም ዓመታት ድህነት ነግሶበት የነበረው ገጠሩ የኦሮሚያ ክፍል የልማት ማዕከል በመሆን ለክልላችንና ለሀገራችን አጠቃላይ ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ አስተዋጽኦ በማድረግና የልማት ጀግኖች መፍለቂያ መሆን ጀምሯል፡፡ የኦሮሚያ ከተሞችም በልማት እየተዋቡ ለኑሮ፣ ለሥራና ለኢንቨስትመንት እጅግ ምቹ እየሆኑ መምጣት የጀመሩ ሲሆን፣ በገጠርና በከተማ መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት በቀጣይነት እየተደረገ ባለው ጥረት የህዝቡ ተጠቃሚነት እያደገ ይገኛል፡፡
በተመሳሳይ መልኩም የማይክሮና ጥቃቅን ድርጅቶች ልማት በማስፋፋት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ነገ ባለሀብት ሊሆኑ የሚችሉ የልማት ጀግኖችን በብዛት ለማፍራትና ለኢንዱስትሪው ልማት አስተማማኝ መሠረት ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ መጥቷል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ የሁሉንም ደረጃ ትምህርት በሁሉም አካባቢ በማስፋፋትና ጥራቱ እንዲጠበቅ ለማድረግ በትምህርት የተቀረጸ፣ ብቃት ያለው፣ የሀገርና የህዝብ ፍቅር ያለውና የተጀመረውን ዕድገት ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚችል አዲስ ትውልድ በብዛትና በጥራት በማፍራት፣ የጤና አገልግሎትን በማስፋፋት ጤንነቱ የተጠበቀ ህብረተሰብ ለማፍራት በድርጅታችን አመራር በተሰራው ሥራ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ከፊታችን ያለውን ብሩህ ተስፋ ከወዲሁ የሚያሳይ እየሆነ መጥቷል፡፡
ድርጅታችን ኦህዴድ በዚህ በተጀመረው የልማትና የዴሞክራሲ ጐዳና ህዳሴ ጉዞ ውስጥ ለሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት በመስጠት የክልላችንን የዕድገት እንስቃሴ ለማሳካት እየሰጠ ባለው አመራር የህዝባችን ኑሮ ደረጃ በደረጃ እየተሻሻለና የሀገራችን መልካም ገጽታም በዓለም ላይ በክብር እየተነሳ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ኦህዴድ የዕድገት እንቅስቃሴውን በይበልጥ ለማሳካት በተለያዩ መስኮች የሚንፀባረቁና ለልማት እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊቶችንና አመለካከቶችን ከምንጫቸው ለማድረቅና የልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚን የበላይነት ለማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደርን ለማጠናከርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማፋጠን ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ እያደረገ ባለው ጥረትም አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ጀምሯል፡፡
በነዚህ ባለፉት ዓመታት በነበረው የትግልና የድል ሂደት ውስጥ ድርጅታችን ሁለንተናዊ ብቃቱን እየገነባ የመጣ፣ የኦሮሞ ህዝብ በአመራሩ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ተስፋ የጣለበትና በላቀ ርብርብ ከጐኑ የሚቆምለት ድርጅት ለመሆን በቅተዋል፡፡
በአጠቃላይ ኦህዴድ እንደሌሎች በኦሮሞ ህዝብ ስም እየፎከሩ፣ ወደኋላ ተመልሰው ያለፈውን የታሪክ ጠባሳ እያከኩ፣ ለህዝቡ ምንም ውጤት ሳያስገኙ ዕድሜ መቁጠር ብቻን እንደ ሥራ ይዘው የቀሩ ድርጅቶች ሳይሆን ተደብቆ የነበረውን የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ወደ ብርሃን ያወጣና ከህዝቡ ጋር ሆኖ በልማት ያሸበረቀ አዲስ ታሪክ እየሰራ ያለ ድርጅት መሆኑን በተጨባጭ ሊያረጋግጥ ችሏል፡፡ ዛሬም ደግሞ በሰራው አኩሪ ተግባር የዛሬ ብቻ ሳይሆን የቀጣዩ ትውልድ ድርጅት መሆኑን ማረጋገጥ የጀመረበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ድርጅታችን በሁሉም መስክ ባደረገው ትግል ውስጥ ስኬታማ እየሆነ የመጣው አካሄዱን በትክክል እየገመገመ ድክመቱን እያስተካከለና ጥንካሬውን በይበልጥ እያስፋፋ፣ ቀጣይነት ባለው የህዝብ ማዕበል ራሱን እያደሰ የሀገራችንን ህዳሴ ከግቡ ለማድረስ በቆራጥነት የሚሰራ ድርጅት በመሆኑ ነው፡፡
ኦህዴድ ሰበብ ፈልጐ ከትግልና ከኦሮሞ ህዝብ ሸሽቶ አያውቅም፤ ለኦሮሞ ህዝብም ጀርባውን ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ችግር ሲያጋጥምም ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ተመካክሮ ህዝቡን በማሳተፍ ችግሩን ይፈታል፡፡ ኦህዴድ የድላችን ምንጭ ህዝቡን ማመንና ለህዝብ መታመን ነው ብሎ ያምናል፡፡ ሰበብ በማብዛትና ዕድሜ በመቁጠር ብቻ ጊዜያቸውን ከጨረሱ ድርጅቶች ለየት ባለ ሁኔታ ለጋ ድርጅታችንን የዚሁ ሁሉ ድል ባለቤት ያደረገው ትልቁ ምስጢር ይኸው ነው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ባለፉት 25 ዓመታት የትግል ጉዞ ውስጥ ሲሰጥ በነበረው ሁሉ አቀፍ አመራር እስካሁን የተሰራው ሥራ በጣም አኩሪና ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ካስቀመጥነው ግብ አንፃር ሲታይ ግን አሁንም ከባድ ሥራ ከፊታችን አለ፡፡ ድርጅታችን ባለፉት ሂደቶች ውስጥ ታላላቅ ድሎችን ማስመዝገቡ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ ውስንነቶችም እንዳሉ በትክክል ይገነዘባል፡፡
የዕድገት ትግሉን ጀመርነው እንጂ አልጨረስነውም፡፡ ከፊታችን ያለው የዕድገት ጉዞ ካለፈው የበለጠና ከባድ ነው፡፡ እስካሁን ባሉት ድሎች እየተጠናከርን አሳድገንና አስረዝመን በማቀድና "መሥራት እንችላለን" የሚል ስሜት ገንብተን የተለጠጡ የልማት ግቦቻችንን ማሳካት እንደጀመርነው፤ አሁንም ካለፈው የበለጠ መጠነ ሰፊና ከባድ ሥራን በቀጣይነት አቅደን በመተግበር ህዳሴያችንን ከግቡ ለማድረስ በቁርጠኝነት መሥራት አለብን፡፡
ስለሆነም ኦህዴድ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ከሰፊው ህዝብ ጋር አክብሮ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር በሚዘጋጅበት በአሁኑ ሰዓት በትግል ሲያፈራ የመጣውን የአመራር ብቃትና ልምድ እጅግ እየሰፋ ከመጣው የህዝባችን የጋለ ተሳትፎ ጋር በማቀናጀትና የተጀመረውን የዕድገት እንቅስቃሴ በማስቀጠል የህዝባችንን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥና የሀገራችንና የክልላችንን ህዳሴ ከግቡ ለማድረስ በቁርጠኝነትና በላቀ የትግል ስሜት የሚረባረብ መሆኑን በድጋሚ ቃሉን ያድሳል፡፡
እንደሚታወቀው ሁሉ ይህ የኦህዴድ 25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓል የሚከበረው 5ኛው ዙር አጠቃላይ ምርጫ በቀረበበት ወሳኝ ሰዓት ላይ ነው፡፡ ድርጅታችን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የብዙሃን ፓርቲ ሥርዓት መንግስት በህዝብ ምርጫና ውሳኔ የሚቋቋምበትና ተጠሪነቱም ለህዝብ የሆነ መንግስት የሚመሰረትበትን ሥርዓት እውን ለማድረግ ከፍተኛ መስዕዋትነት የከፈለ ስለሆነ የዘንድሮም ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አመኔታ ያለው ሆኖ እንዲካሄድ ለማድረግ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህም በአንድ በኩል እንደማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት በምርጫው አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ለማሸነፍ እየተወዳደረ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን ላይ እንዳለ ድርጅት ለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ምርጫው እየገነባነው ያለውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕድገት በትክክል ሊያሳይ በሚችል ደረጃ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርና በኦህዴድ/ኢህአዴግ የአመራር ህዳሴ የተጀመረውን ጉዞ ቀጣይነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ በሚያስችል አኳኃን በድል እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ለምርጫው ራሱን በማዘጋጀት ቀርቧል፡፡ ኦህዴድ በታማኝነት ለያዘው ህዝባዊ ዓላማና የህዝቡን ፍላጐትና ጥቅም ለማረጋገጥ በከፈለው ክቡር መስዕዋትነት በግልጽ የሚታይ ውጤት ሲያስመዘግብ የመጣ እንደመሆኑ መጠን አሁንም በእሱ አመራር በስኬት ጐዳና እየተራመደ ያለውን የዕድገት እንቅስቃሴ በቆራጥነት ለማስቀጠል መላው የኦሮሚያ ህዝብ በድጋሚ እንደሚመርጠው ያለውን ሙሉ ተስፋ በዚህ አጋጣሚ ይገልፃል፡፡
የተከበራችሁ የኦሮሞ ህዝቦች
ድርጅታችን የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በሁሉም የትግል ምዕራፍ ውስጥ በሀገራችንና በክልላችን በተከታታይነት ለተመዘገቡ የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ውጤቶች ስኬት የአመራር ድርሻውን ሲወጣ የመጣው ከሁሉም በላይ ህዝባችን በድርጅቱ መስመር ተሰልፎ፣ በድርጅቱ የተቀረጹ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በውል ተረድቶ ፣በአስተሳሰብና በተግባር አንድ ሆኖ፣ ተስማምቶ፣ ተደራጅቶና ተባብሮ ለዕድገት መረባረብ ስለቻለ ነው፡፡ አሁንም ታሪካችንንና፣ ቋንቋችንንና ባህላችንን በይበልጥ ለማሳደግና በልማት ጠንክረን በማንነታችን በላቀ ደረጃ ለመኩራት የምንችለው በድርጅታችን አመራር የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ በማስቀጠል በፍጥነት ወደፊት መራመድ ስንችል ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ የክልላችን ህዝብ በሙሉ የስርዓቱን ቀጣይነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥና የተጀመረውን የዕድገት እንቅስቃሴ እጅግ በማጠናከር የሀገራችንን ራዕይ ለማሳካት እንዳለፈው ሁሉ በዚህ ምርጫም ኦህዴድን በመምረጥ ክንዳችሁን አስተባብራችሁ፣ ከላይ እስከታች በመደራጀት በእልህና በአንድነት ስሜት ለዕድገት እንድትረባረቡ ኦህዴድ ጥሪውን ሲያስተላልፍላችሁ በእናንተ ላይ ያለውን ሙሉ እምነት ዳግም ያረጋግጣል፡፡
የተከበራችሁ የሀገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣
ኦህዴድ/ኢህአዴግ የሀገራችን ህዝቦች በሙሉ በእኩልነት፣ በመፈቃቀርና በመከባበር የምንኖርባት የበለጸገችና ዴሞክራሲያዊነት ኢትዮጵያን ለመገንባት በግንባር ቀደምነት እየታገለ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ ስለሆነም እስከዛሬ ድረስ አንድ ሆነን ሀገራችንን ለማልማትና ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን ለማጠናከር፣ አንድ ክንድ ሆነን አብረን ለማደግና ለመጠቀም በህብረት ስንንቀሳቀስ እንደነበርነው ሁሉ አሁንም በቀጣዩ የዕድገት ትግል ውስጥ ካለፈው በበለጠ አንድነታችንንና ስምምነታችንን አጠናክረን ተጨማሪ ድል ለመጐናጸፍ እንድትረባረቡና የኦህዴድ/ኢህአዴግን ትክክለኛ መስመር በመምረጥ ለህዳሴው ጉዞ ቀጣይነት ዋስትናነታችሁን እንድታረጋግጡ ኦህዴድ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል፡፡
የተከበራችሁ የድርጅታችን ደጋፊዎች፣
ድርጅታችን በሂደት እየተጠናከረና በሁሉም የትግል መስክ ውስጥ ድል እያስመዘገበ እስከዛሬ ለመድረሱ የደጋፊዎቹ ርብርብ እጅግ ወሳኝ የሆነ ሥፍራ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ እስከዛሬ የህዝባችንን መብትና ጥቅም ለማስከበር አንድ ሆነን በመቀናጀት ባሳለፍናቸው የትግል ምዕራፎች ሁሉ በመረባረብና ትግሉ የሚጠይቀውን መስዕዋትነት ሁሉ አብረን በመክፈል በአሸናፊነት እንደመጣን ሁሉ አሁንም የሀገራችንና የክልላችንን ህዳሴ በሚያሳካ ቀጣይ ትግላችን ውስጥ ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብ በህብረት መንቀሳቀሱን እንድትቀጥሉበትና ይህን 5ኛውን ዙር አጠቃላይ ምርጫም በድርጅታችን አሸናፊነት ለማጠናቀቅ በእልህ እንድትንቀሳቀሱ ኦህዴድ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል፡፡
የተከበራችሁ የኦህዴድ አባላትና ታጋይ ጓዶች
የምንገኝበት ወቅት ወሳኝ ሰዓት ነው፡፡ ስለዚህ ድርጅታችን ባሳለፈው ውጣ ውረድ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆናችሁ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዕዋትነት በቁርጠኝነት ስትከፍሉ እንደመጣችሁ ሁሉ ዛሬም ካለፈው በበለጠ እንደብረት ተጠብቀን ራሳችንን በማጠናከር የድርጅታችንን ተልዕኮ ለማሳካትና የዘንድሮ ምርጫ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሆኖ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድና ድርጅታችን የተጀመረውን የዕድገት ጉዞ ለመምራት የህዝቡን ይሁንታ በድጋሚ የሚያገኝበት ምርጫ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ህዝባችንን ከዳር እስከዳር በማንቀሳቀስ ካለፈው በበለጠ እንድትረባረቡ ኦህዴድ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
በዚህ አጋጣሚም ድርጅታችን የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በዚህ ወሳኝ ሰዓት ላይ የሚጠበቅበትን የአመራር ድርሻ በብቃት ለመወጣት ከመቼውም በላይ ዝግጁ መሆኑን እያረጋገጥን ቀጣዩ ጊዜ የስኬት፣ የደስታ፣ በድርጅታችን አመራር እየተካሄደ ባለው የዕድገት ትግል ተጨማሪ ድል የምናስመዘግብበት ጊዜ እንዲሆንልን ያለውን ምኞት ይገልፃል፡፡
ዘላለማዊ ክብር በትግሉ ለተሰው ሰማዕታት !!
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ
መጋቢት 16 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም
ፊንፊኔ

No comments:

Post a Comment