Friday, 27 March 2015

ታላቁ መሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ በ2002 ምርጫ ማግስት ድምፃችን ይከበር ብሎ በነቂስ ወጥቶ በመስቀል አደባባይ ለተሰበሰበው ህዝብ ካደረጉት አይረሴ ንግግር፡-




እኛ ኢህአዴጎች ህዘቡ በነጻ ሞክራሲ ውሳኔው ለሰጠን ይሁንታ እጅግ እናመሰግናለን ፡፡ የአገራችን ሴቶች መቼም ቢሆን የድርጅታችን የጀርባ አጥንት በመሆን እስካሁን ባገኙት የእኩልነት መብት ላይ በመመስረት ለላቀ ውጤት ለመታገል በድምጻቸው መወሰናቸውን በእጅጉ አናደንቃለን ፤እናመሰግናለም፡፡
የአገራችን ወጣቶች ባለፉት አመታት በተገኘው ልማት ተጠቃሚ የሆኑ ብቻ ሳይሆኑ ውጤቱንም ለማጣጣም በስራ ፈላጊነት የሚጠባበቁትን ቢሆኑ የችግራቸው መፍትሄ የድርጅታችን መስመር መሆኑን ተገንዝበው በአስገራሚ ደረጃ ይሁኝታቸውን ስለሰጡን በእጅጉ እናመሰግናለን፤እንኮራባቸውማለን፡፡
በምርጫው አመትም ቢሆን አማራጭ የሌለውን የመንግስት ግብር መክፈል አለባችሁ ብለን አጥብቀን የያዝናቸው ከዛም አልፈን በአንዳንድ የአፈፃፀም ስህተቶቻችን ቅር ያሰኘናቸው ባለሃብቶች ሳይቀሩ ድርጅታችን ከስህተቶቹ የሚማርና ጉድለቶቹን የሚያስተካክል ድርጅት መሆኑን ተገንዝበው ለሰጡን ድምፅና ድጋፍ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
ከሰፊው የከተሞቻችን ህዝብም ባሻገር መላው የአርሶ አደር ህዝባችን እንደ ወትሮው ራሱንና ድርጅታችንን እንደማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች አድርጎ በመቁጠር የማይናወጥ አቋሙን በድጋሚ በምርጫ ካርዱ በማረጋገጡ የሚሰማን ክብርና ድስታ ወሰን የለውም ፡፡

የአዲስ አበባ ህዝብ በማንኛውም ወቅት ለህዝቡ ድምፅ ያለንን ክብርተመልክቶ ቅሬታ የሚፈጥሩበትን ጉድለቶቻችንን ለማረም ያለንን ቁርጠኝነትና ገና በቀጣይ ማስተካከል ያለብን ነገሮች እንደተጠበቁ ሆኖ ያስመዘገብነውን ድልና ውጤት ተገንዝቦ ከአምስት አመት በኋላ ብይኑን እንደገና በነፃ ምርጫው ሰጥቶናል፡፡የአዲስ አበባ ህዝብ ድምፁን ሲነፍገንም ሆነ ድምፁን ሲሰጠን ከመብትና ጥቅሙ በመነሳት እጅግ ፍትሃዊ የሆነ ብይን የሚሰጥ ህዝብ እንደሆነ በተግባር አረጋግጧል፡፡የመጨረሻውና ፍትሃዊ ዳኛ ለሆነው ህዝባችን ያለንን ክብርና ምስጋና በድጋሚ ለመግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
በዘንድሮው ምርጫ የአዲስ አበባ ህዝብና በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ህዝብ ለኢህአዴግ ጥረትና የስራ ውጤት እውቅና ከመስጠት አልፎ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የማያሻማ መልእክት አስተላልፏል ብዪ አምናለሁ፡፡ህዝብን ለማገልገል የሚያስችል ራእይ ይዞ ከመንቀሳቀስ ይልቅ የጭፍን ጥላቻ ፖለቲካን ማስተናገድ እንደማይፈልግ፤የህዝብ ጥቅምን ሳይሆን የቂም በቀልና ቁርሾ አላማን የሚያራምድ ፖለቲካን ማየት እንደማይፈልግ፤ከሁሉም በላይ ደግሞ በምርጫ ሽፋን የአንድ ሰው ህይወትም ቢሆን መክፈል እንደማይፈልግ በውል አቋሙን ገልጿል ብዪ አምናለሁ፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከድርጅታችን ልምድ ሊወስዱት የሚገባ ትምህርት ያለ ይመስለኛል፡፡የህዝቡን ብይን ሰበብ አስባብ ሳይፈልጉ በፀጋ ሊቀበሉ፤ህዝብ ያልወደደላቸው ነገር ምን እንደሆነ በሰከነ አእምሮ አጢነው ለማስተካከል ቆርጠው ቢነሱ ህዝቡ ፍትሃዊ ዳኛ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስመስክሯልና በሚቀጥለው ጊዜ ውጤታቸውን አይቶ ሊክሳቸው እንደሚችል ሊገነዘቡ ይገባል እላለሁ፡፡እናም እስካሁን ድረስ ይህንኑ ገንቢ አቅጣጫ ለመከተል ለወሰኑት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለኝን አድናቆት እየገለፅኩ ሌሎቹም ይህንን ፈለግ እንዲከተሉ በህዝቡ ስም እጠይቃለሁ፡፡በከፊል መገለፅ በጀመረው የምርጫ ውጤት እንደታየው ህዝቡ ድምፅ እንደነፈጋቸው በፀጋ በመቀበል የዚህን ኩሩ ህዝብ ብይን ከቶውንም ተፈፃሚነት በማይኖረው የውጭ ሃይሎች ይግባኝ ሰሚነት ለመሸርሸር ከመሞከር እንዲቆጠቡና ለራሳቸውና ለህዝባቸው ውሳኔ ተገቢውን ክብር እንዲሰጡ አሳስባለሁ፡፡
እስካሁን ድረስ በነበረው ሂደት አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ከማናችንም የተሰወረ አይደለም፡፡በምርጫው እለት ታዛቢ ተወካዮቻቸው

ባለፈው ምርጫ ምርጫችንን በመታዘብ ከወገንተኝነት ነፃ ሆነው እንዲመሰክሩ እምነታችንን የጣልንባቸው ታዛቢዎች ወገን ለይተው ሊፋለሙና በእሳት ላይ ነዳጅ ሲያርከፈክፉ በከፍተኛ ቁጭት ተመልክተናል ፡፡ ወዳጅና አጋር እንዲሆኑን የተመኘናቸው አንጋሽ መሆን ሲከጅላቸው ፣የኢትዮጵያ ፖለቲካ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት መሆን ሲቃጣቸው በከፍተኛ ሃዘን ተመልክተናል ፡፡ አሁንም ያለፈው አልፏል ፡፡ በዚህ ኩሩ ህዝብ የወዳጅነትና አጋርነት እጆች አሁንም እንደተዘረጀጉ ናቸው ፡፡ የህዝቡን መሪዎቹን የመምረጥ ሉዓላዊ ስልጣን አክብሩ ፣ ለህዝቡ ውሳኔና ድምፅ ተገቢውን ክብር ስጡ እንላለን ፡፡
የተከበራችሁ የሰላምና የዴሞክራሲ ሰልፈኞች !   
በዘነድሮው ምርጫ ህዝባችን እስካሁን ከተገለፀው ጊዜያዊ ውጤት በመነሳት ይሁንታን እንደሰጠን ግልፅ ቢሆንም ይሁንታቸውን ያልሰጡን ዜጎቻችን እንዳሉም እንገነዘባለን ፡፡ የመረጠንን ህዝብ ድምፅና ውሳኔ እንደምናከብር ሁሉ ያልመረጠንን ህዝብ ድምፅም እንደምናከብር ያለአንዳች ማወላወል ለመግለፅ እወዳለሁ ፡፡ እናም ይሁንታችሁን ያልሰጣችሁንን ዜጎች ቅር ያሰኘንበትን ምክንያት አጥንተን ለማስተካከል እንደምንረባረብ ፣ በሚቀጥለው ጊዜ ይሁንታችሁን ለማግኘት ሌት ተቀን እንደምንጣጣር እስከዚያው ድረስ ደግሞ የምናቋቁመው መንግስት የመረጠንን ህዝብ ብቻ ሳይሆን እናንተንም በእኩልነት እንደሚያገለግል በድርጅታችን መላ አባላትና ሰማዕታት ስም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ፡፡
ምንም አንኳ ህዝባዊ አላማችንና የተደራጀ ርብርባችን ባስገኘልን ታላቅ ህዝባዊ ድጋፍ የምንኮራና የምንደሰት ብንሆንም ህዝቡ እጅግ ከባድ ሃላፊነት በላያችን ላይ እንደጫነም በሚገባ እንገነዘባለን ፡፡ ምንም አንኳ በጥረታችንና በውጤታችን ህዝባችንን በማርካታችን ብንደሰትም አሁንም ህዝባችንን ቅር የሚያሰኙ በርካታ መሰረታዊ ጉድለቶች እንዳሉብን በጥልቀት እንገነዘባለን ፡፡ ስለሆነም በዛሬው የዴሞክራሲ ፌሽታ እለት እኛ ኢህአዴጎች ድምጽ ለሰጠንም ሆነ ላልሰጠን ፍትሃዊ ዳኛ ህዝባችን ያለንን ጥልቅ አክብሮትና ምስጋና በድጋሚ ከልብ እንገልፃለን ፡፡
ምንም እንኳ የምርጫውን ውጤት ሙሉ በሙሉ ከማወቃችን በፊትም ቢሆን በሚቀጥሉት አምስት አመታት የህዝባችንን ፍላጎት ያረካሉ ብለን የቀየስናቸው አቅጣጫዎችና እቅዶች ያሉን ቢሆንም ያገኘነውን እጅት ሰፊ የህዝብ አደራ ታሳቢ በማድረግ እነዚህን እቅዶች ለመተግበር ከመረባረብ ጎን ለጎን የሰጣችሁንን ከፍተኛ ሃላፊነት በይበልጥ መለወጣት ከነገው እለት ጀምሮ እቅዶቻችንን በዝረዝር ፈትሸን መከለስ እነደምንጀምር ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ ፡፡በዚህ አጋጣሚ ያገኘነው ከግምታችን በእጅጉ የላቀ ውጤት ተጨማሪ ከባድ ሸክም ያሸክመን እንደሆነ እንጂ እንደማያኩራራን እንደገና ላረጋጥጥላችኑ እፈልጋለሁ ፡፡
 በምርጫው ያልተሳካላችሁ ተቃዋሚዎች ሁሉ የህዝቡን ድምፅና ውሳኔ ተቀብላችሁ የአገሪቱን ህገ-መንግስትና ህጎች አክብራችሁ እስከተንቀሳቀሳችሁ ድረስ የምክር ቤት ወንበር ቢኖራችሁም ባይኖራችሁም በሁሉም ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች እናንተን ለማማከርና ለማሳተፍ ቃል እንገባላኋላን፡፡ይህን ቃል የምንገባላችሁ በአገራችን የተሃድሶ ትግል አጋር መሆን እደምትችሉና እንደሚገባችሁ ስለምናምን ብቻ ሳይሆን ፣ ምንም ያህል ቁጥር ይኑራቸው ድምፃቸውን ለእናንተው የሰጡ ዜጎች በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍና የመደመጥ መብት እነዳላቸው ጠንቅቀን ስለምናውቅ ጭምር ነው ፡፡ በዛሬው ምርጫ አሸናፊው ይህኛው ወይም ያኛው ድርጅት ሳይሆን አሸናፊው የኢትዮጵያ ህዳሴ ፣አሸናፊው የኢትዮጰያ ዴሞክራሲና የኢትዮጵያ ህዝቦች በመሆናቸው ድሉ የሁላችንም ነው፡፡በመሆኑም ለመላው መራጭ ህዝባችንና የአገራችን የሰላምና የዴሞክራሲ ሃይሎች ከልባችን እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን ፡፡
በድጋሚ በሉዓላዊው የመሾምና የመሻር ስልጣናችሁ ፊት ከአምስት ሚሊዮን በላይ የምንሆን የኢህአዴግ አባላትና ሰማዕታት በታላቅ ትህትና ምስጋናችንን እንገልፃለን ፡፡ እጅ እንነሳለን

No comments:

Post a Comment