ሰማያዊ ፓርቲ፤ ምርጫን እንደታክቲክ አመፅን እንደስትራቴጂ
ክፍል 1
**********************
ክፍል 1
**********************
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሃይሎች ክንዳቸውን አስተባብረው ዋነኛ ጠላታቸው በሆነው ድህነት ላይ በመዝመት የድህነትን አስጠሊታ ገፅታ ለመደምሰስ ከፍተኛ ትግል በማድረግ ላይ መሆናቸው ለሁሉም ግልፅ ነው፡፡ ኢህአዴግ በዚህ አኳያ በመጫወት ላይ የሚገኘው ከፍተኛ አዎንታዊ ሚናም ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህንን አልዋጥ ያለው ፅንፈኛው ሃይል ከሞትከኩ ሰርዶ አይብቀል ከሚል የእንስሳዋ መርሆው በመነሳት በመገንነባት ላይ ባለው የሃገሪቱ ዴሞክራሲ ስርዓትና የልማት ትራንስፎርመሽን ላይ ሰደድ እሳት በማቀጣጠል ዶግ አመድ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል፡፡
ስለሆነም እንደስትራቴጂ ሁሉንም የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስኬትን የሚያኮላሹ መንገዶችን ለመጠቀም ያስችለው ዘንድ እንደታክቲክ በምርጫው ሂደትን መቆየትን መርጧል፡፡ የፅንፈኛው ሃይል አውራ እኔ ነኝ ብሎ ራሱን በራሱ የሾመ ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ወደ ምርጫ የገባው አንድም የኢትዮጵያ ህዝብ በምዝገባ ባሳየው ንቅናቄ ተደናግጦ ሁለትም በምርጫ ሂደቱ ውስጥ በመግባት የምርጫ ሂደቱን ለማደናቀፍ እንደ አንድ ስልት መጠቀም ስለፈለገ ነው፡፡ ይህንን ስልቱም በግላጭ እያሳየን ነው፡፡
በምርጫ ህግ መሰረት በአንድ ምርጫ ክልል ምን ያህል ፓርቲዎች መወዳደር አለባቸው የሚለው ህግ የወጣ ሰማያዊ ፓርቲ የሚባለው ሳይፈጠር ብቻ ሳይሆን ሳይጠነነሰስ የወጣ መሆኑ እየታወቀ አባሎቻቸው/አውራቸውን ጨምሮ/ በዕጣ ከተወዳዳሪነት መውጣታቸው /በነገራችን ላይ የሌሎች ፓርቲዎች ጭምር በዕጣ ከውድድር ውጪ የሆንበትና የሰማያዊ ዕጩዎች ያለፉበት ቦታም አለ/ ሆን ተብሎ ሰማያዊ ፓርቲን ከውድድር ለማስወጣት የተዘየደ አዲስ አሰራር አድርገው ለማደናገር እየሰሩ ነው፡፡ ሰሙኑ ከአውሮፓውያኑ በፅ/ቤታቸው ባደረጉት ‹‹ምክክርም›› አንድ ጮኽ ብለው ያላዘኑት ጉዳይ 200 አባሎቻችን ሆን ተብሎ እንዳይወደደሩ ተደርጓል የሚል ነው፡፡ የሚሉትን ያህል ቁጥር በሙሉ በአንድ ምርጫ ክልል በህግ ከተወሰነው በላይ ተወዳዳሪዎች በመቅረባቸው በወጣ ዕጣ የተወገዱ አይመስለኝም፡፡ እንዲያ ከሆነ በእርግጥም ፓርቲው እግረ ደረቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ነገር ግን ፓርቲው ወደ ምርጫ የገባ ምርጫን ስትራቴጂካሊ የትግል አማራጭ ነው የሚል ከልብ ተቀብሎ ሳይሆን እንደትግል ስልት /አመፅ ማካሄጃ/ ስለሆነ በእያንዳንዷ ተግባር ከመንግስት ተቋማትን የሚያጨቋጭቁ ጥሰቶችን ሆን ብሎ እየፈፀመ ይገኛል፡፡ በዕጪዎች ምዝገባ የታየውም ይህ ነው፡፡ በርካታ የሌላ ፓርቲ አመራሮች የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎች አድርጎ አቅርቧል፡፡ አንድ ሰው ደግሞ በአንድ ግዜ የአንድ ፓርቲ አባል ነው መሆን ያለበት፡፡ በተለይ ደግሞ የአንድ ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ፣ ስራ አስፈፃሚ፣ ፕሬዝዳንት በጉባኤ ካልተሰናበተ ወይም ራሱ በግልፅደብዳቤ መልቀቁ አስቀድሞ ሳያሳውቅ የሌላ ፓርቲ ተወዳዳሪ ሆኖ መቀረበ አይችልም፡፡ ይህ የተፃፈ ህግ መጥቀስም ሳያስፈልገ ማንም ሰው የሚገነዘበው አመክንዮ ነው፡፡
አንድ ፓርቲ ከሌላ ፓርቲ የሚለይበት የራሱ ዓላማና ፕሮግራም አለው ተብሎ የታሰባል፡፡ የፓርቲው አመራር ደግሞ ይህንን የፓርቲው ዓላማ ለማሳካት በአባላቱ የተመረጠ ነው፡፡ ይህንን ሃላፊነት የተሰጠው ሰው ለሌላ ፓርቲ እወዳደራለሁ ካለ መጀመሪያውንም ከፓርቲው ነው መልቀቅ ያለበት፡፡ ወይም ደግሞ ለአባላቱ አቅርቦ ፓርቲው ፈርሶ ከሌላው ፓርቲ እንዲወሃድ ወይም ግንባር ፈጥሮ በአንድ ፕሮግራም እንዲመራ ማድረግ አለበት፡፡ በአንድ ጊዜ የሁለት ፓርቲ አባል መሆን ግን ተቀባይነት የለውም ብቻ ሳይሆን በህግም ያስጠይቃል፡፡ ሰለዚህ ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህ ሰዎች የሌላ ፓርቲ አመራሮች መሆናቸው እየታወቀ የራሱ ተወዳዳሪ አድርጎ ማቅረቡ መጀመሪያኑ ህገወጥ መሆኑንና ከምርጫ ቦርድ እንደሚያጨቃጭቀው አጥቶት የፈፀመው ቴክኒካል ስህተት አይደለም፡፡ አስቦና አልሞ ሆን ብሎ ምርጫ ቦርድን ቅርቀራ ውስጥ አስገባበታለሁኝ፣የምርጫው ተቀባይነት አደፍርስበታለሁኝ፣ የውጭ ሃይል ትኩረት ለመሳብ እጠቀምበታለሁኝ ብሎ የተከተለው ስልት ነው፡፡ በዚህ ስልት ምንያህል አተረፈ ራሱ ያውቀዋል፡፡
ነገርግን ጉዳዩ በተናጠል ሳይሆን ምርጫን እንደስልት አመፅን እንደስትራቴጂ ከያዘው ዕቅድ ጋር ነው አስተሳስረን መገንዘብም መመዘንም ያለብን፡፡ ይህ ፓርቲ የሌላ ፓርቲ አመራሮች ፍቃደኝነታቸው ዕጩ አድርጎ ማቀረቡ ብቻ ሳይሆን በርካታ የሌላ ፓርቲ አባላት / በተለይም የአንድነት ፓርቲ/ ካለፍቃዳቸውና እውቅናቸው ጭምር ነው ዕጩ አድርጎ አስመዝግቦ የተገኘው፡፡ በርካታ ዕጩዎች የተሰረዙም በዚህ ምክንያት አጭበርብሮ ያስመዘገባቸው ነው፡፡ ይህ አይን ያወጣ ህገወጥ ተግባር የግለሰቦችን መብት የሚጋፋ በመሆኑ ግለሰቦቹ በህግም ሊጠይቁት ይገባል ብዬ አምናለሁኝ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የአንድነት ፓርቲ አባሎቼና መዋቅሬን ሰማያዊ ፓርቲ አላግባብ ተጠቅሞባቸዋል ብሎ ባቀረበው ቅሬታ ተጣርቶ እንዲሰረዙ ተደርገዋል፡፡ እንግዲህ እነዚህንና የመሳሰሉ የህግ ጥሰት በመፈፀሙ ናቸው ዕጭዎቹ እንዲሰረዙ የተደረጉ፡፡ 200 መሆናቸው በቁጥሩ ላይ መረጃ ባይኖረኝም፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ፤ ምርጫን እንደታክቲክ አመፅን እንደስትራቴጂ ይዞ እስከ ግንቦት ይቀጥላል፡፡ የተቀረፀው ነፃ ዴሞክራሰያዊ ፍትሃዊና በህዝብ ተአማኒነት ያተራፈ የምርጫ ስትራጂ ግን የሰማያዊ ፓርቲና የቀለም አብዮት ስትራቴጂስቶችን ታክቲክንም ስትራቴጂም የማክሸፍ ዓቅም አለው፡፡ እናም የዘንድሮ ምርጫ የኢህአዴግ አሸናፊነት ብቻ ሳይሆን የቀለም አብዮት አራማጆች ምኞት እስከወዲያኛው የሚቀበርበት ይሆናል፡፡ የሰላም ሃይሎች ከነውጥ ሃይሎች ይበልጥ አሸናፊዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም የሰላም ሃይሎች የትክክለኛ ዓለማ ባለቤቶች ናቸው እና፡፡ እነሱም ኢህአዴግና የኢትዮጵያ ህዝብ ናቸው፡፡
No comments:
Post a Comment